ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በህገወጥ መልኩ የገቡ ስደተኞችን ወደመጡበት እንደሚባርሩ ቃል መግባታቸው ይታወሳል
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር የትኞቹን ስደተኞች ከአሜሪካ ሊያባርር ይችላል?
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ ከሁለት ሳምንት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያካሄደች ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈዋል፡፡
የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ የብዙዎች ትኩረት የሆነው ጥር ላይ ስራ የሚጀምረው አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ምን ይመስላል ሚለው ሆኗል፡፡
በተለይም ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ለአሜሪካዊያን ቃል ከገቡባቸው ጉዳዮች መካከል የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው እና በአሜሪካ ከተሞች የሚኖሩ ስደተኞችን አባርራለሁ ማለታቸው አንዱ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም በአሜሪካ የሚኖሩ ነገር ግን የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ተገደን ልንባረር እንችላለን የሚል ስጋት ውስጥ እንደሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ወንጀል ያልፈጸሙ እና ተቀጥረው ከሚያገኟት ገቢ ላይ ግብር እየከፈሉ በመሆናቸው በአዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ላይባረሩ እንደሚችሉ የሚያስቡ ስደተኞችም ቀላል አይደሉም ተብሏል፡፡
ይሁንና የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ህገወጥ ስደተኞች ናቸው ተብለው በተለዩ ነዋሪዎች ላይ ቀድሞ የሚያባርራቸው አልያም የሚቆዩ ስደተኞች በሚል የሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ እንደማይኖር በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በአሜሪካ የስደተኞች ምክር ቤት የፖሊሲ ዳይሬክተር የሆኑት አሮን ሜልኒክ እንዳሉት አሜሪካ ከገቡ በኋላ ወንጀል አለመስራት ወይም ግብር መክፈል ላለመባረር ምክንያት አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ የድንበር ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ቶም ሀውክ በበኩላቸው የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ለአሜሪካዊያን ስጋት በመሆናቸው ይባረራሉ ብለዋል፡፡
የትራምፕ የነጩ ቤት የመጀመሪያ ቀን እና የህገወጥ ስደተኞች እጣ ፈንታ
ጥር 20 በሚጀምረው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ውስጥ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚሆኑት ዲጄ ቫንስ በበኩላቸው በመጀመሪያው ዙር አንድ ሚሊዮን ስደተኞች እንደሚባረሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በአሜሪካ አሁን ላይ 13 ሚሊዮን ህገ ወጥ ስደተኞች ያሉ ሲሆን በዜግነት አሜሪካዊን የሆኑ 5 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ የመኖሪያ እና ስራ ፈቃድ ከሌላቸው ቤተሰቦች የተወለዱ ናቸው ተብሏል፡፡
ይሁንና ዶናልድ ትራምፕ ካቢኔያቸውን በማቋቋም ስራ የተጠመዱ ሲሆን እስካሁን በይፋ ምን ያህል እና የትኞቹን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው እንደሚመልሱ አላሳወቁም፡፡