ስዊድን ሀገሪቷን ለቀው ለሚወጡ ስደተኞች 34 ሺህ ዶላር እከፍላለሁ አለች
መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በስደተኞች የሚፈጸሙ ከባባድ ወንጀሎች በእጥፍ በመጨመራቸው ነው
ስደተኞች በሚፈጽሟቸው ወንጀሎች የተሰላቸችው ዴንማርክ በተመሳሳይ ይህን አካሄድ እየተከተለች ነው
ስዊድን ሀገሪቷን ለቀው ለሚወጡ ስደተኞች 34 ሺህ ዶላር ልትከፍል ነው፡፡
የሀገሪቷ የኢሜግሬሽን ሚንስትር ጆን ፎርሲል ከ2026 ጀምሮ ሀገሪቷን ለቀው ለሚወጡ ስደተኞች እስከ 34 ሺህ ዶላር ድረስ ለመክፈል ተዘጋጅተናል፤ ይህ የሆነው አዲስ በተዘጋጀው የስደተኞች ፖሊሲ ለውጥ ነው ብለዋል፡፡
በ2015 ላይ ከተለያዩ የአለም ክፍሎች ለሚመጡ ጥገኝነት ጥያቄዎች ድንበሯን ክፍት አድርጋ የነበረችው ሀገር በዚሁ አመት ከ160 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላለች፡፡
አብዘሀኞቹ ስደተኞች ከመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ መነሻቸውን ያደረጉ ናቸው፡፡
በርካታ ስደተኞችን ከመቀበል ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ እየጨመሩ የሚገኙት ከባባድ ወንጀሎች መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ እንዳስገደደው ተነግሯል፡፡
ከ2012 እስከ 2023 በሀገሪቱ የሚፈጸሙ የግድያ ወንጀሎች በእጥፍ ጨምረዋል በተመሳሳይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች በ56 በመቶ ሲጨምሩ ወንጀሎቹ 90 በመቶ የሚፈጸሙት በስደተኞች መሆኑን መንግስት አስታውቋል፡፡
የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትር ኦልፍ ክሪስተርሰን ባለፈው አመት በ12 ሰአታት ልዩነት ውስጥ 3 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የስደተኞች ወንጀል ለመከላከል አዲስ አሰራር እንደሚከተሉ ቃል ገብተው ነበር፡፡
ከዚህ ባለፈም በአደንዛዥ እጽ ሽያጭ ፣ በተደራጁ ወንጀሎች እና በሌሎችም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ሲሳተፉ የተገኙ ስደተኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ መጡበት እንደሚመልሱ ዝተዋል፡፡
ኤርትራዊያን በስዊድን ስቶኮለም ጎራ ከፍለው መደባደባቸው ተገለጸ
በሀገሪቷ የሚንቀሳቀሱ የቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ መንግስት እሰጠዋለሁ ያለው ገንዘብ ላይ ጭማሪ እንዲያደርግ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የስዊድንን እሴቶች ስደተኞች እያጠፉ ይገኛሉ በሚል በጥብቅ እየሞገቱ የሚገኙት እነኚህ ፓርቲዎች የገንዘብ መጠኑ ከፍ ቢደረግ ጥያቄውን ተቀብለው ከሀገር ለመውጣት ፈቃደኛ የሚሆኑ በርካታ ስደተኞች ይኖራሉ ብለዋል፡፡
ዴንማርክ በተመሳሳይ ምክንያት ጥብቅ የስደተኞች ፖሊስ በመከተል ላይ ከሚገኙ የአካባቢው ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
ሀገሪቷን ለቀው ለሚወጡ ስደተኞችም እስከ 22ሺ ዶላር ድረስ በመክፈል ላይ ትገኛለች