ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ወደ ጦር ግምባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ
እውነተኛው ጦርነት ኢንስታግራም ላይ አይደለም ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ስለ ጦርነቱ አስተያየት እሚሰጡትን ተችተዋል
ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን በአንድ ቀን እቋጨዋለሁ ማለታቸው ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ወደ ጦር ግምባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ።
ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን ለሁለት ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል መላኳን ተከትሎ የተጀመረው ሁለት ዓመት ሊሞላው አንድ ሳምንት ብቻ ቀርቶታል።
በዓለም ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ያስከተለው ይህን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ ከሽፈዋል።
ከወራት በኋላ በሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ዋነኛ እጩ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ ይህን ጦርነት እንደሚያስቆሙት ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ጦርነት ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት ሙነሻ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል አቋም ያላቸው ሲሆን አሜሪካንን የበለጠ ይጎዳልም ብለዋል።
አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠው ገንዘብ እና ጦር መሳሪያ ስህተት ነው የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ አስተያየታቸው በፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ አልተወደደላቸውም።
በጀርመን ሙኒክ የደህንነት ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ዶናልድ ትራምፕን ወደ ጦር ግምባር ጋብዘዋል።
"ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን ያሉ የጦር ግምባሮችን እንዲጎበኙ እጋብዛለሁ፣ እኔም አብሬያቸው ለመሄድ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
"ጦርነት በኢንስታግራም አይመራም" ያሉት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጦርነቱ እንዲቆም የመወሰን ስልጣን ያለው ማን እንደሆነ ለህዝብ ማሳየት ይኖርብናል ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካ ምክር ቤት ለዩክሬን ሊለገስ በተዘጋጀ 60 ቢሊዮን ዶላር ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት እስካሁን አልተሳካም።
ፕሬዝዳንት ባይደን አሜሪካ ለዩክሬን ልትሰጠው ያሰበችው 60 ቢሊዮን ዶላር በሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ምክንያት በወቅቱ ባለመድረሱ ሩሲያ አቭዲቭካን ከኪቭ ሙውሰዷን ተናግረዋል።