የትጥቅ እጥረት ያጋጠማት ዩክሬን ወታደሮቿን ከአቭዲቭካ ከተማ አስወጣች
የዩክሬን አዲሱ የጦር አዛዥ የሀገሪቱ ጦር በሩሲያ ከበባ ውስጥ ገብቶ ከባድ ጉዳት ከማስተናገዱ በፊት ከተማዋን ለቆ እንዲወጣ አዘዋል
አቭዲቭካ ከባክሙት በመቀጠል ለሩሲያ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላት ከተማ መሆኗ ተገልጿል
የዩክሬን ወታደሮች ከአቭዲቭካ ከተማ ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተገለጸ።
የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርይስኪ በሩሲያ ጦር ከበባ ውስጥ ከመግባት ለመዳን ውሳኔውን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።
በምስራቃዊቷ የዩክሬን ከተማ ላለፉት አራት ወራት በተካሄደ ጦርነት ዩክሬን ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዷ የተነገረ ሲሆን፥ ሞስኮ በጦር መሳሪያም ሆነ በወታደሮች ብዛት ብልጫውን መያዟም ተመላክቷል።
በሩሲያ ወደተያዘችው ዶኔስክ መግቢያ በር የሆነችው አቭዲቭካ ለወራት በተካሄደው ጦርነት ፈራርሳለች፤ ከ34 ሺህ በላይ ሰዎች መኖሪያ በነበረችው ከተማ አሁን 1 ሺህ ገደማ ሰዎች ይኖሩባታል ተብሏል።
ከባክሙት በመቀጠል ለሩሲያ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ እንዳላት የተነገረላት ከተማ በሞስኮ ወታደሮች መያዟ ከተነገረ ቢቆይም ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ከተማ ድረስ በመዝለቅ አልተያዘችም ሲሉ ማስተባበላቸው ይታወሳል።
“ወታደሮቻችን የሩሲያን ጦር ለማውደም የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል” ያሉት አዲሱ የዩክሬን ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርይስኪ፥ ሩሲያ ድል እንዳደረገቻቸው በይፋ ባይገልጹም “ወታደሮቻችን ከከበባ ለመታደግ ወጥተናል” ብለዋል።
የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባዩ ጆን ኪርቢ በበኩላቸው የዩክሬን ወታደሮች የትጥቅ ችግር ስለገጠማቸው ከአቭዲቭካ ከተማ ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ነው የተናገሩት።
የአሜሪካ ሴኔት ባለፈው ሳምንት ለዩክሬን ያጸደቀው የ60 ቢሊየን ዶላር በህዝብ ተወካዮች ምክርቤቱም ጸድቆ በፍጥነት ለኬቭ ሊደርስላት ይገባልም ብለዋል።
ዩክሬን ሁለተኛ አመቱን ከቀናት በኋላ በሚይዘው ጦርነት ከምዕራባውያን የምትጠባበቀው ድጋፍ በፍጥነት አለመድረሱ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዋን ወደኋላ እንዳስቀረው ገልጻለች።
የሰሜን አትላልቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግም የአሜሪካ ድጋፍ መጓተት በአውደ ውጊያዎች ላይ ተጽዕኖውን እያሳረፈ እንደሚገኝ መናገራቸውን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
የጀርመኑ ኬል ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው አሜሪካ ከየካቲት 2022 እስከ ታህሳስ 2023 ለዩክሬን 45 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አድርጋለች (በወር ሁለት ቢሊየን ዩሮ ገደማ)።
የአውሮፓ ህብረትና 27ቱ አባል ሀገራትይ ጦርነቱ እንደጀተመረ 49 ነጥብ 7 ቢሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸው እስካሁን 35 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ የሚያወጣ ወታደራዊ ድጋፍ አድርገዋል።
ይህ ሁሉ ድጋፍ በጦርነቱ ላይ የሩሲያን ግስጋሴ ከመግታት ውጭ የተያዙባትን ስፍራዎች ማስለቀቅ ያላስቻላት ኬቭ ተማጽኖዋን ቀጥላለች፤ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪም ወደ ጀርመን አቅንተዋል።