ዩክሬን ያጋጠማት የመሳሪያ እጥረት ሩሲያ እንድታሸነፍ እድል እየሰጠ ነው ብለዋል
የዩኩሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘሌንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት የጦር መሳሪያ እጥረት እንጋደጠማት አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ በጀርመን በተካሄደ ኮንፈርንስ ላይ ባደረጉት ንግግር “ዩክሬንን ያጋጠማት የጦር መሳሪያ እጥረት ሰው ሰራሽ ነው” ብለዋል።
እንዲህ አይነቱ የጦር መሳሪያ እጥረት ሩሲያ እንድታሸንፍ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስታወቁት።
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በአውሮፓ ውስጥ ያለውን "አስከፊ" ሁኔታን ለማስወገድ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች አስቸኳይ እንዲቀርብላቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
በጦር ግንባር ያሉ የዩክሬን ወታሮች ትጥቅ እያለቀባቸው ነው የተባለ ሲሆን፤ ይህ ያጋጠመውም በአሜሪካ ኮንገረስ ያሉ የትራምፕ ደጋፊዎች ለዩክሬን እንዲደርስ የቀረበውን የመሳሪያ ድጋፍ ማእቀፍ በመያዛቸው ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ፤ “ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዩክሬን ከመጣ አብሬው ወደ ጦር ግባር በመሄድ ላስጎበኘው ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
ይህም “ትክክለኛው ጦርት በኢንስታግራም ላይ ሳይሆን ትክክለኛው ጦርነት በዩክሬን ውስጥ እንደሆነ ለማሳየት ነው” ሲሉም ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
ከትጥቅ እጥረት ጋር ተያይዞ የዩክሬን ወታደሮች ከአቭዲቭካ ከተማ ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ይታወሳል።
የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርይስኪ በሩሲያ ጦር ከበባ ውስጥ ከመግባት ለመዳን ውሳኔውን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።