የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር በኢራን ላይ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል ተገለጸ
ለኢራን ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው በሚባለው ነዳጅ ምርቷ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች ይጣላሉ ተብሏል
ኢራን በበኩሏ ዶናልድ ትራምፕ በቴህራን ላይ የያዙትን አቋም እንዲያስተካክሉ ጠይቃለች
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር በኢራን ላይ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል ተገለጸ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካ 47ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ወር በኋላ ስልጣን እንደሚረከቡ ይጠበቃል፡፡
ኢራን ለአሜሪካ ጥቅም ስጋት በመሆኗ ጫና ሊደረግባት ይገባል ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን እንደያዙ የመጀመሪያ ስራቸው አዲስ ማዕቀብ መጣል ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ዎል ስትሪት ጆርናል የዶናልድ ትራምፕ አማካሪዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ሲጀምሩ በመካከለኛው ምስራቋ ኢራን ላይ ጫና መፍጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ብለዋል፡፡
ትራምፕ በተለይም ለኢራን ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነው የነዳጅ ምርቷ ዋነኛ ኢላማ ሊደርግ ይችላል የተባለ ሲሆን ቴህራንን ከዓለም ገበያ መነጠል እና ወታደራዊ እርምጃዎችን ጭምር ሊከተሉ ይችላሉም ተብሏል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ኢራንን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ “አቋሜ ግልጽ ነው ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቅ አትችልም” ብለው ነበር፡፡
አሜሪካ ትራምፕን ለመግደል አሲሯል ባለችው ኢራናዊ ላይ ክስ መሰረተች
ኢራን በበኩሏ ዶናልድ ትራምፕ በቴህራን ላይ የያዙትን የጫና ፖሊሲ መከተል እንዲተው አሳስባለች፡፡
የኢራን የቁልፍ አጋርነት ጉዳዮች እና ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ጃቫድ ዛሪፍ እንዳሉት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ኢራንን አስመልክቶ ይከተሉት የነበረውን ፖሊሲ እንዲቀይሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዛሪፍ አክለውም በኢራን ላይ የተሳሳተ ፖሊሲ መከተል የተሳሳተ ውጤት እንዲመጣ አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን አሁን ያለው ሁኔታ ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ላይ ከቆዩበት ጊዜ መለወጡን የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል፡፡
ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ያላት ተጽዕኖ መጨመሩን፣ ከዚህ በፊት ግጭት ውስጥ ከነበረችባቸው ሀገራት ጋር የነበራት ግንኙነት መቀየሩ፣ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ያላት ግንኙነት መሻሻሉ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች መቀየራቸውን ተናግረዋል፡፡