እስራኤል ከአሜሪካ 25 “ኤፍ-15” የውጊያ ጄቶችን ልትገዛ ነው
የእስራኤል ጦር 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡት ዘመናዊ ጄቶች ለመግዛት ከቦይንግ ጋር ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል
የቦይንግ “ኤፍ-15” ጄቶች በሚሸከሙት ክብደት፣ በሚያካልሉት ርቀትና በፍጥነታቸው የዘመኑ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ ውጤት ናቸው ተብሏል
እስራኤል በአሜሪካ ድጋፍ የቀጣዩ ትውልድ “ኤፍ-15” ተዋጊ ጄት ባለቤት ለመሆን ተቃርባለች።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር 25 “ኤፍ -15” ጄቶችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል።
የቦይንግ ዘመኑን የዋጁትና የቀጣዩ ትውልድ ”ኤፍ-15” ጄቶች “ኤፍ-15ኢኤክስ” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡት ጄቶች ግዥ የአሜሪካ ኮንግረንስ በዚህ አመት ለእስራኤል ያጸደቀው ድጋፍ አካል መሆኑንም ሚኒስቴሩ በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ አመላክቷል።
የጦር ጄቶቹ የእስራኤል የአየር ሃይል በመካከለኛው ምስራቅ ቀዳሚነቱን ያስቀጥላሉ የተባለ ሲሆን፥ አሁንም ሆነ ወደፊት በቀጠናው ለሚገጥሙ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዙም ተገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ቦይንግ “ኤፍ -15” ጄቶቹን ለእስራኤል ከ2031 ጀምሮ ማቅረብ ይጀምራል፤ በየአመቱም ከአራት እስከ ስድስት ጄቶችን አጠናቆ ያስረክባል።
“ኤፍ-15 ጄቶቹ በዚህ አመት ከገዛናቸውና (በሊባኖስና ጋዛ) ጦርነት ውጤታማነታቸውን ካሳዩን ኤፍ-35 ጄቶች ጋር ሲጣመሩ የእስራኤልን የአየር ሃይል አቅምና ተደራሽነት ይበልጥ ያጠናክሩታል” ብለዋል የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ኢያል ዛሚር።
የቦይንግ “ኤፍ-15” ጄቶች (“ኤፍ-15ኢኤክስ”) በሚሸከሙት ክብደት፣ በሚያካልሉት ርቀትና በፍጥነታቸው የዘመኑ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ ውጤት ናቸው ተብሏል።
ለየትኛውም የውጊያ አውሮፕላን ሽፋን የሚሰጡ የጀርባ አጥንት ይሆናሉም ነው ያለው ቦይንግ በድረገጹ ባሰፈረው መግለጫ።
“ኤፍ-15ኢኤክስ”
- እስከ 13 ሺህ 300 ኪሎግራም የሚመዝኑ የጦር መሳሪያዎችን መሸከም ይችላል
- 12 መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ይሸከማል
- በስአት 3 ሺህ 581 ኪሎሜትሮችን ይጓዛል (የአለማችን ፈጣኑ የውጊያ ጄት ያደርገዋል)
- ዘመናዊ ራዳር፣ ሴንሰሮች እና የኮሙዩኒኬሽን መሳሪያዎች ተገጥመውለታል
- በየትኛውም የአየር ሁኔታ፤ በቀንም ሆነ በምሽት ጥቃት ማድረስ ይችላል
- በአሜሪካ ሚዙሪ ግዛት ሴንት ሊዩስ ከተማ ይመረታል
- በየካቲት 2021 የሙከራ በረራ አድርጓል
- በ2023 ሙከራውን አጠናቆ በሰኔ ወር 2024 በአሜሪካ ኦሪገን በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል
- እስካሁን የ“ኤፍ-15ኢኤክስ” ጄት ብቸኛዋ ተጠቃሚ አሜሪካ ናት
- ቦይንግ የውጊያ መሃንዲስ ነው የተባለለትን ጄት ለፖላንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ለመሸጥ ንግግር ጀምሯል