በመጋቢት ወር የፓሪስ አበዳሪ ሀገራት ስብስብ ሶማሊያ ከተበደረችው 2 ቢሊዮን ዶላር 99 በመቶውን እዳ እንደሚሰርዝ አስታውቋል
ሶማሊያ ከአሜሪካ የተበደረችው ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያልተከፈለ እዳ እንደሚሰረዝላት አስታውቃለች፡፡
ገንዘቡ በዚያድ ባሬ መንግስት የስልጣን ዘመን የተወሰደ ብድር ሲሆን የሀገሪቱን ቀሪ ዕዳ ሩቡን የሚሽፍን ነው ተብሏል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ሀገሪቷ ባልተረጋጋ እና በጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት በተወሰዱ ብድሮች እና ተከፍለው ሊያልቁ በማይችሉ የወለድ ክፍያዎች ከፍተኛ ጫና ውጥ ትገኛለች ብለዋል፡፡
የሶማሊያ የገንዘብ ሚንስትር ቢሂ ኢማን ኢጌህ በበኩላቸው “አሜሪካ የሞቃዲሾን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና እድገት ለመደገፍ እያደረገች ለምትገኝው ድጋፍ ምስጋናችንን እንገልጻለን” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
“ሀገሪቱ ከዚህ በኋላ ተጠምጥመውባት ከነበሩ ሰንሰለቶች በመላቀቅ ኢኮኖሚዋን ለማሻሻል ትሰራለችም” ነው ያሉት
በሳምንቱ መጀምርያ አሜሪካ ለመሰረዝ ቃል የገባቸው የ1.14 ቢሊየን ዶላር በተከታታይ የሶማሊያን ብድር ለመሰረዝ ቃል መግባቷን ተክቶሎ የተደረገ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) መረጃ መሰረት ሞቃዲሾ በሁለትዮሽ ስምምነት ከምታገኛቸው ብድሮች የዋሽንግተን ድርሻ አንድ አምስተኛውን ይሸፍናል፡፡
በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ሪቻርድ ራይሊ ሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት ከተበደረችው 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የአሜሪካ መሆኑን ገልጸው የእዳ ስረዛው ከባድ ዕዳ ላለባቸው ደሀ ሀገራት የብድር ይቅርታ ለማድረግ በአይኤምኤፍ በተዘጋጀው ማዕቀፍ መሰረት ገቢራዊ የሚሆን ነው ብለዋል ፡፡
በተጨማሪም ከአሜሪካ እና ከአጋሮች በተገኘ ድጋፍ ሶማሊያ ማሻሻያዎችን፣ አዳዲስ የፋይናንስ ህጎችን በማውጣት በገንዘብ ረገድ ተጠያቂነትን ለመተግበር ጥረት እያደረገች መሆኗን ነው የገለጹት፡፡
በ2023 የአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ በከፍተኛ የእዳ ጫና ውስጥ የሚገኙ ሀገራትን እዳ ለማቃለል እና ከአለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማስቻል በጋራ ባዘጋጁት ማዕቀፍ ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል ሶማሊያ አንዷ ነች፡፡
በተመሳሳይ በመጋቢት ወር የአለማችን ሀብታም አበዳሪ ሀገራት ቡድን “የፓሪስ ክለብ” ሶማሊያ ከቡድኑ ከተበደረችው 2 ቢሊዮን ዶላር 99 በመቶውን እዳ እንደሚሰርዝ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
በዓለም ባንክ መረጃ መሰረትም ይህ የሶማሊያ የውጭ ብድርን በ 2018 ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ ከነበረው 64 በመቶ ድርሻ በ 2024 መጀመርያ ወደ 6 በመቶ ዝቅ እንዲል አስችሏል፡፡