የአሜሪካ ኩባንያዎች በዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን ለመጠገን እንዲሰማሩ ተፈቀደ
መሳሪያዎችን ለመጠገን ጨረታ ያሸነፉት ኩባንያዎቹ በዩክሬን እንዲሰማሩ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ሲጠባበቁ ቆይተዋል
ተሰናባቹ የጆ ባይደን አስተዳደር የሰጠውን ፈቃድ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ሊሰርዙት ይችላል እየተባለ ነው
የጆ ባይደን አስተዳደር የአሜሪካ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች በዩክሬን ለጦር መሳርያ ጥገና እንዲሰማሩ ፈቅዷል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ተቋራጮች ወደ ዩክሬን መሰማራት ላይ የነበረው እገዳ መነሳቱን ሮይተርስና ሲኤንኤን የፔንታጎን ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡
ጨረታ ተወዳድረው ያሸነፉት እና በቅርቡ በዩክሬን ይሰማራሉ ተብለው የሚጠበቁት ኩባንያዎች ለሰራተኞቻቸው ደህነንት ሀላፊነት እንደሚወስዱ ተነግሯል፡፡
እያንዳንዱ ድርጅት በሩሲያ በሚፈጸም ጥቃት ሰራተኞቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የደህንነት እና የአደጋ ቅነሳ እቅዶችን በጨረታቸው አካቶ አቅርቧል፡፡
በጦርነቱ በቀጥታ አይሳተፉም የተባሉት የመከላከያ ድርጅቶች ከጦር ግንባር ርቀው የጦር መሳርያዎችን ጥገና ላይ የሚሰማሩ ሲሆን ሰራተኞቹን የሚጠበቁ የታጠቁ የደህንነት አካላት አብረዋቸው ይጓዛሉ፡፡
ተሰናባቹ አስተዳደር ተፈጻሚ ያደረጉትን መመሪያ የአሜሪካውያንን ህይወት በውጭ ሀገር ጦርነት አደጋ ውስጥ ላለማስገባት ቃል የገቡት ትራምፕ ፈቃዱን ሊሰርዙት እንደሚችሉ ይጠብቃል፡፡
አሜሪካ እና የኔቶ አጋሮቿ “ኤፍ-16” ተዋጊ ጄቶችን ጨምሮ ሌሎች የተራቀቁ አሜሪካ ሰራሽ የጦር መሳሪያዎችን በሰፊው ለዩክሬን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም በውግያ ላይ ጉዳት የሚደርስባቸው እና የሚበላሹ መሳሪያዎችን ለመጠገን እንዲሁም ድጋሚ ወደ ስራ ለመስገባት ለዩክሬን ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡
“ኤፍ-16” የውጊያ ጄት እና “ፓትሮይት” የተባለው የሚሳይል ሲስተም ተቋራጮቹ ትኩረት ከሚያደርጉባቸው የጦር መሳርያዎች መካከል ቀዳሚዎቹ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም የተበላሹ መሳሪያዎችን ወደ ፖላንድ እና ሮማኒያ በመላክ የሚደረገውን የጥግና ሂደት በማስቀረት መሳርያዎችን በቶሎ በመጠገን የዩክሬን ጦር በተሻለ አቅም ወደ ጦር ግንባር እንዲመለስ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ግጭት ውስጥ የኔቶ ወታደሮች ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ እንደሚያወቁ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ኤቲኤሲኤምኤሲ እና ስቶርም ሻዶ ያሉ አሜሪካ እና አጋሮቿ ለኪቭ ያቀረቧቸው በርካታ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ስርአት ያላቸው ሚሳይሎች በኔቶ አባል ሀገራት ወታደሮች እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ ጦር በዩክሬን በሚገኙ የጥገና ተቋማት ላይ የአየር ድብደባዎችን በየጊዜው ያደርጋል፤ በዚህ ሳምንት ብቻ በዩክሬን ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ፣ ወታደራዊ መሰረተ ልማቶች እና የጥግና ማዕከላት ላይ 38 ጥቃቶችን አድርጓል ።