ትራምፕ በንግድ እና ኢኮኖሚ ዙሪያ ከቻይና ጋር መደራደር እንደሚፈልጉ ገለጹ
አዲሱ ፕሬዝዳንት ስልጣን በያዙ የመጀመሪያው ቀን በቻይና ምርቶች ላይ የ60 በመቶ ታሪፍ ገቢራዊ ለማድረግ ይዘውት የነበረውን እቅድ አዘግይተዋል
ከትራምፕ በዓለ ሲመት አንድ ቀን በኋላ የሩስያ እና የቻይና መሪዎች በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ በበይነ መረብ ተወያይተዋል
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባልተጠበቀ ሁኔታ በቻይና ጉዳይ የተለሳለሰ አቋም አሳይተዋል፡፡
ስልጣን በያዙ የመጀመሪያ ቀን በቻይና ምርቶች ላይ የ60 በመቶ ታሪፍ ጨማሪ እንደሚያደርጉ ሲዝቱ የሰነበቱት ፕሬዝዳንቱ በንግድ እና ኢኮኖሚ ጉዳይ ከቤጂንግ ጋር መምከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ከተሾሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር አሜሪካን ይበልጥ ባለጸጋ እናደርጋታለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዋሽንግተንን ይበልጥ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ድረድሮች ላይ ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን በ2020 የንግድ ስምምነት ያልተፈቱ ጉዳዮች ለቀጣይ እርምጃዎች ፈተና ቢሆኑም ፤ ትራምፕ የሁለተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ ቤጂንግ እና ዋሽንግተን ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ አዲስ ፍኖተ ካርታ እንደሚያስፈልጋቸው ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ትራምፕ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ ጋር በፍሎሪዳ እና ቤጂንግ ለሁለት ጊዜ ተገናኝተው ቢመክሩም፤ ከተከታታይ የንግድ ጦርነት ውስጥ ከመግባት አላገዳቸውም። ይህም የአለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለትን ላይ እክል ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ ሁለቱም ወገኖች ካቆሙበት ለመቀጠል ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም በምትኩ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ እና ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያመለክቱ ምልክቶች እየታዩ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በምረጡኝ ቅስቀሳቸው በቻይና ጉዳይ ጠንካራ አቋም ሲያንጸባርቁ መቆየታቸውን የእስያ ፓስፊክ ዋና ኢኮኖሚስት አሊሺያ ጋርሺያ ሄሬሮ ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል፡፡
አክለውም “ትራምፕ ስምምነት ይፈልጋ፤ ይህ ባይሆን ኖሮ የታሪፍ ጭማሪውን በመጀመሪያ የስልጣን ቀናቸው ተግባራዊ ያደርጉ ነበር” ብለዋል።
እ.ኤ.አ. በ2018 ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይና ላይ ከተጣለው ታሪፍ የበለጠ የአሁኑ ታሪፍ ሀገሪቱን ተጎጂ የሚያደርጋት እንደሚሆን ተንታኙ ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ የነበረው ታሪፍ በቻይና የንብረት ግብይት ላይ ተጽዕኖ ከማሳረፉም በላይ የስራ አጥነት በ16 በመቶ እንዲጨምር እና የአክስዮን ገበያ እንዲዋዥቅም ምክንያት ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት የቻይናው ፕሬዝዳንት እና ትራምፕ በዋና ጉዳዮች ላይ ስልታዊ የግንኙነት መስመር ለመፍጠር በስልክ መስማማታቸው ይታወሳል።
ከቀጥታ የውሳኔ እርምጃ ለድርድር ክፍት የሆነ አካሄድ ለመከተል መወሰናቸው ደግሞ የተፈራውን የንግድ ጦርነት ሊያስቀር እንደሚችል ይታመናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትራምፕ በዓለ ሲመት አንድ ቀን በኋላ በበይነ መርብ የተወያዩት የሩስያው ፕሬዝዳንት እና የቻይናው አቻቸው በአለም መረጋጋት ዙሪያ የጋራ እርምጃዎችን ለመውሰድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡