ዶናልድ ትራምፕ ወደ ትዊተር የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ተናገሩ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብጥብጥ በመቀስቀስ ከማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ታግደው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጅ አዲሱ የትዊተር ባለቤት ኢሎን ማስክ ባሰባሰቡት የህዝብ አስተያየት መሰረት ከ15 ሚሊዮን (51.8 በመቶብ) በላይ የሚሆኑ የትዊተር ተጠቃሚዎች ትራምፕ ወደነበሩበት እንዲመለሱ የድጋፍ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም የትዊተር ባለቤት ኢሎን ማስክ "ህዝቡ ድምጹ ሰጥተዋል እናም ትራምፕ ወደነበሩበት ይመለሳሉ” ሲሉ ማስክ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ትዊተር ተጠቃሚዎች የትራምፕ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ መመለስ ቢሹም ግን ትራምፕ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ትዊተር የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ጥር 8 ቀን 2021 ከመታገዱ በፊት ከ88 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች የነበረው የትራምፕ የትዊተር አካውንት ተከታዮችን ማሰባሰብ የጀመረ ሲሆን ቅዳሜ እለት በ10 ሰአት ላይ ወደ 100ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ጨምሯል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በእለቱ ብዙም ፍላጎት ሳይኖራቸው ብቅ ብለው ነበርም ተብሏል።
በወቅቱ በሪፐብሊካን የአይሁድ ጥምረት አመታዊ የአመራር ስብሰባ ላይ የነበሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወደ ትዊተር ለመመለስ ሃሳብ ይኖራቸው ይሆን ተብለው ሲጠየቁም "ለዚህ ምንም ምክንያት አይታየኝም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከትዊተር ይልቅ የተሻለ ተሳትፎ በሚያደርጉበት በትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ በተዘጋጀው አዲሱ ፕላትፎርም “ትሩዝ ሶሻል አፕ” ላይ እንደሚቆዩም ተናግረዋል።
ትዊተር በትራምፕ ምላሽ ላይ አስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2024 ወደ ነጩ ቤተመንግስት ዋይት ሀውስን በድጋሚ ለመመለስ ጉዞ ላይ የሚገኙት ትራምፕ ኢሎን ማስክን ቢያሞካሹም በትዊተር ከበቂ በላይ መሰቃየታቸው ገልጸዋል፡፡
አዲሱ የትዊተር ባለቤት ማስክ በመጀመሪያ በግንቦት ወር በትራምፕ ላይ የተጣለውን እገዳ ለመቀልበስ ማቀዳቸው አስታውቀው እንደነበር አይዘነጋም፡፡