ፌስቡክ እና ትዊተር “አሳሳች” ያሉትን የትራምፕ ጽሁፍ ከገጻቸው ማስወገዳቸውን አስታወቁ
ፕሬዝዳንቱ ከኮቪድ ነጻ መሆናቸው ካልተረጋገጠ ቀጣዩን ክርክር እንደማያደርጉ ጆ ባይደን ገልጸዋል
ቫይረሱ አሁንም በኋይት ሀውስ መሰራጨቱን ቀጥሏል
ፌስቡክ እና ትዊተር “አሳሳች” ያሉትን የትራምፕ ጽሁፍ ከገጻቸው ማስወገዳቸውን አስታወቁ
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ኮቪድ-19 ከጉንፋን የተለየ እንዳልሆነ በመግለጽ የለጠፉትን ጽሁፍ ሕብረተሰቡን የሚያሳስት በሚል ማንሳታቸውን ፌስቡክ እና ትዊተር አስታውቀዋል፡፡
ፌስቡክ ፕሬዝዳንቱ የለጠፉትን ያውርድ እንጂ የለጠፉት ጽሁፍ ከመውረዱ በፊት ወደ 26,000 ጊዜ ያህል በሌሎች ገጾች ተጋርቷል፡፡
የኩባንያው ቃል አቀባይ “እኛ ስለ ኮቪድ-19 ክብደት የሚለጠፍ የተሳሳተ መረጃን እናስወግዳለን” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
ከሶስተኛ ወገን የእውነት ማጣሪያ መርሃግብሩ ፖለቲከኞችን ነፃ የሚያደርገው በዓለም ትልቁ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያ በሪፐብሊካኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽሁፎች ላይ እስካሁን እምብዛም እርምጃ አልወሰደም፡፡
ትዊተርም በተመሳሳይ ማክሰኞ ዕለት በፕሬዝዳንቱ ጽሁፍ ላይ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ “ከ ኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ አሳሳች እና ሊጎዱ የሚችሉ መረጃዎችን በማሰራጨት” የኩባንያውን ደንቦች እንደጣሱ በመግለጽ ጽሁፋቸው በሌሎች ግለሰቦች ገጽ ላይ እንዳይጋራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) በዚህ ዓመት መጀመሪያ በአሜሪካ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ ከ 210,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ይህም በዓለም ላይ ከፍተኛው የሞት ቁጥር ነው፡፡ ከ7.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ሀገሪቱ በዚህም ዓለምን በቀዳሚነት ትመራለች፡፡
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ ሰኞ ምሽት ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ቫይረሱን እንዳትፈሩት ፤ እንዲቆጣጠራችሁ አትፍቀዱለት በሚል ያስተላለፉት መልዕክት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ቫይረሱ የተገኘባቸው በፕሬዝዳንት ትራምፕ ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች አሁንም እየተለዩ ነው፡፡ ስቴፈን ሚለር የተባለ የኋይት ሀውስ አማካሪ እንዲሁም እንዲሁም አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተዘግቧል፡፡ ይህን ተከትሎም በርካታ ወታደራዊ ሹማምንት ራሳቸውን አግልለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ትራምፕ ቫይረሱ ካልለቀቃቸው በስተቀር በቀጣይ ክርክር ማድረግ እንደሌለባቸው ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ገልጸዋል፡፡ “እስካሁንም ኮቪድ ያለበት ይመስለኛል ፤ በመሆኑም ክርክራችንን ማድረግ የለብንም” ያሉት ባይደን በህክምና ባለሙያዎች ተመርተው እንደሚወስኑ ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ቀጣይ ክርክር ከሳምንት በኋላ እንደአውሮፓውያኑ ጥቅምት 15 በሚያሚ ፍሎሪዳ ሊካሔድ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡