በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አሁንም “በአንክሮ” መከታተሉን እንደሚቀጥል ትዊተር አስታወቀ
አነጋጋሪ የኢትዮጵያ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበትን አምድ (ትሬንድስ) ለጊዜው የዘጋው ትዊተር የማስታወቂያ ስራዎች መቆማቸውንም ነው የገለጸው
ትዊተር በኢትዮጵያ የተጠቃሚዎቹን እና መሬት ላይ ያሉ ሰዎችን ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ ትኩረቱ እንደሆነ አስታውቋል
በወቅታዊ ጉዳዮች ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ገደቦችን የጣለው ትዊተር አሁንም ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው አለ፡፡
ትዊተር በማህበረሰብ ትስስር ገጹ የሚለቀቁ የመረጃዎችን ደህንነት ማስጠበቅ አሁንም ቀዳሚ ትኩረቴ ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተለዋዋጭ መሆኑን በማስታወስ በገጹ የሚጋሩ አንዳንድ ይዘቶች መሬት ላይ የወረደ ተጨባጭ ተጽዕኖዎች እንዳላቸው አስታውቋል፡፡
እንዲህ ዐይነት ጎጂ ተጽዕኖ ያላቸውን ይዘቶች እንዴት ባለ መንገድ ያን ያህል ጎልተው እንዳይታዩ እንደሚያደርግም አስቀምጧል ትዊተር በመግለጫው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊነትን በማጥላላት ሁከትን እና መድልዎን በሚያበረታቱ የጥላቻ ንግግሮችና ይዘቶች ላይ የነቃ ግምገማን አደርጋለሁ ነው ያለው፡፡
ይህን በሚያደርግበት ወቅት መርሆዎቹን በሚዛናዊና ፍትሃዊነት ለመተግበር ከማለም በላይ ለተጠቃሚዎቹ እና መሬት ላይ ላሉ ሰዎች ደህንነትነ ቀዳሚ ትኩረትን እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚፈጸመው የሳይበር ጥቃት 90 በመቶው በግንዛቤ ጉድለት የሚያጋጥም ነው
በድርጊቶች ላይ ተመስርቶ መሬት ላይ ያለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እርምጃዎችን እንደሚወስድም ነው ያስታወቀው፤ አቤቱታዎችን ተቀብሎ ውሳኔዎቹን ሊቀለብስ እንደሚችል በመግለጽ፡፡
በኢትዮጵያ በዋናነት የሚያነጋግሩ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበትን አምድ (ትሬንድስ)፣ መልዕክቶችን (ትዊትስ) ለማጋራትና ለመጋራት የሚቻልባቸውን የቡድንና ሌሎች ዝርዝሮችን (ሊስት) እና ማስታወቂያዎችን ማቆሙን በማስታወቅም ደህንነቱ የተጠበቀ ፍለጋን ለማድረግ የሚያስችል አዲስ አገልግሎት መጀመሩንም አስታውቋል፡፡
ማህበራዊ ገጹን ለብዝበዛ የሚዳርጉ ሁኔታዎችን እና ለሰብዓዊ ሰራተኞች ጭምር አደጋ ሊደቅኑ የሚችሉ ጎጂ ይዘቶችን መከታተሉን እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቀው፡፡
ታማኝ ካላቸው የተለያዩ የሃገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አጋር ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር እርምጃውን እንደወሰደም አስቀምጧል በመግለጫው፡፡
ትዊተር ጥቂት የማይባሉ ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያንን ‘አካውንት’ በመዝጋት እንቅስቃሴያቸውን እየገደበ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ከሰሞኑ በርክተው ተደምጠዋል፡፡
በተለይ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ መንግስት ለመጻፍና ለመናገር የሚደፍሩ ጸሃፊዎችን አግዷልም ነበር ሲባል የነበረው፡፡ በተጨባጭ ያገዳቸው ገጾችም አሉ፡፡
ትዊተር ብቻ አይደለም ፌስቡክ ጭምር፤ በእንዲህ ዐይነት ተግባራት ላይ መሰማራቱን ‘አካውንታችን ተዘጋ፤ ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ ተከታዮቻችን ጋር እንዳይደረስ ተደረገ’ በሚል ብዙዎች ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ትዊተር ከፖለቲካዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ ወገንተኝነት ነጻነኝ ሲል በመግለጫቸው አስቀምጧል፡፡