ዶናልድ ትራምፕ ከአራት ዓመት በኋላ ዳግም ፕሬዝዳንት ሆነዋል
ዶናልድ ትራምፕ በይፋ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ፈጸሙ።
ከሁለት ወር በፊት በተካሄደው የአሜሪካው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ በይፋ ስልጣን ተረክበዋል።
ከስምንት ዓመት በፊት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ፈጽመው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ተሸንፈው ስልጣናቸውን ለጆ ባይደን አስረክበው ነበር።
ከአራት ዓመት ዕረፍት በኋላ ዳግም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ አመሻሽ በይፋ ቃለ መሀላ ፈጽመው ስልጣን ከተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተረክበዋል።
በዶናልድ ትራምፕ ቃለ መሀላ ላይ የቀድሞ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ የሀገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እባ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ወጣቱ የምርጫ አጋራቸው የነበሩት ጄ ቫንስ ደግሞ 50ኛው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በቃለ መሀላው ወቅት የአሜሪካን ሀያልነት እመልሳለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ስልጣን በያዙ የመጀመሪያው ቀን "አምባገነን እሆናለሁ" ማለታቸው ይታወሳል።
ስልጣን በያዙበት በዛሬው ዕለት ያደርጓቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ውሳኔዎች መካከል ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደመጡበት ሀገር እንዲባረሩ መወሰን፣ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር የተላለፉ ውሳኔዎችን መሻር፣ የዩክሬን ጦርነትን ማስቆም የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ እና መሰል እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ይጠበቃል።