በዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተጋበዙ የዓለም ሀገራት መሪዎች እነማን ናቸው?
ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን ሰኞ በይፋ ስራ ይጀምራሉ
የዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ለየት ባለ መልኩ እንደሚካሄድ ተገልጿል
በዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተጋበዙ የዓለም ሀገራት መሪዎች እነማን ናቸው?
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን ሰኞ በይፋ ስራ ይጀምራሉ።
ፕሬዝዳንቱ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ከመግባታቸው በፊት በይፋ በዓለ ሲመታቸው የሚከበር ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ላይ በርካታ እንግዶች እንዲገኙ ተጋብዘዋል።
ከተጋበዙት ውስጥም የሀገራት መሪዎች፣ የዓለማችን ባለጸጋዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ይገኛሉ ተብሏል።
ትራምፕ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ከጋበዟቸው የሀገራት መሪዎች መካከል አብዛኞቹ የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች እንደሆኑ ፖለቲኮ ዘግቧል።
ለአብነትም የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ዣቬር ሜሊ፣ የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ኦርባን፣ የኤልሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ፣ የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ቦልሴናሮ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ከአውሮፓ ሀገራት በኩል የፈረንሳይ፣ጀርመን እና ብሪታንያ የቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሪዎች በዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል።
ከባለጸጋዎች ደግሞ ኢለን ሙስክን ጨምሮ ማርክ ዙከርበርግ፣ ጄፍ ቤዞፍ፣ ቢል ጌትስ እና ሌሎችም የአውሮፓ እና እስያ ባለጸጋዎች የተጋበዙ ሲሆን እንደሚገኙም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ከእስያ ደግሞ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ እንዲገኙ በትራምፕ የተጋበዙ ቢሆንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን እንደሚልኩ ይጠበቃል።
ከአፍሪካ እስካሁን በይፋ በዶናልድ ትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተጋበዘ መሪም ሆነ የኢንቨስትመንት ሰው ስለመኖሩ አልተጠቀሰም።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮንደርሊን በትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ አለመጋበዛቸው ብዙዎችን አስገርሟል።
ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን በያዙበት ዕለት በርካታ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል።
ከነዚህ መካከልም የስደተኞች ጉዳይ፣ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር ዘመን የተላለፉ የተወሰኑ ውሳኔዎችን መሻር እና ሌሎች አነጋጋሪ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፉም ይጠበቃል።