ትራምፕ ጾታ የቀየሩ አትሌቶች በሴቶች ስፖርት ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚከለክሉ አስታወቁ
ትራምፕ ወንዶችን ከሴቶች ስፖርት ለማስወጣት እርምጃ ወስዳለሁ ብለዋል
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ቀናቸው በርካታ ውሳኔ እንሚያሳልፉ ይጠበቃል
47ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን በዛሬው እለት ስልጣን የሚረከቡት ዶናልድ ትራምፕ ጾታ የቀየሩ አትሌቶች በሴቶች ስፖርት ላይ እንዳይሳተፉ እንደሚከለክሉ አስታወቁ።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው እለት ባደረጉት ንግግር የፕሬዝዳንቱን ስልጣን ከያዙ በኋላ “ወንዶችን ከሴቶች ስፖርት ለማስወጣት እርምጃ ወስዳለሁ” ብለዋል።
ትራምፕ ጾታ የቀየሩ አትሌቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ የተናሩት በዋሽንትገትን ዲሲ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ባድረጉት ንግግር ነው ተብሏል።
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎች ከወዲሁ ማነጋገራቸውን ቀጥለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ጾታቸውን የቀየሩ 15 ሺህ የአሜሪካ ጦር አባል ወታደሮችን ከስራ እንደሚያግዱ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ሰዎች ተፈጥሯዊ ጾታዎችን መቀየር የለባቸውም ብለው የሚያምኑት ዶናልድ ትራምፕ ጾታቸውን የቀየሩ እና የሀገሪቱ ጦር አባላት የሆኑ ወታደሮችን ከስራ እንደሚያግዱ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተፈጥሯዊ ጾታቸውን የቀየሩ አሜሪካዊያን የሀገሪቱን ጦር መቀላቀል እንዳይችሉ እገዳ እንደሚጥሉም ተገልጿል።
ዶኔልድ ትራምፕ በከ2016-2020 ድረስ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው ዓመታት ውስጥ ተፈጥሯዊ ጾታቸውን የቀየሩ ዜጎች የአሜሪካ ጦርን እንዳይቀላቀሉ እገዳ ጥለው የነበረ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህንን እገዳ አንስተውታል።