የዩክሬን አጋሮች በሰሜን ኮርያ ጉዳይ ቆመው ከመመልከት ወጥተው እርምጃ እንዲወስዱ ዘለንስኪ ጠየቁ
ፕሬዝዳንቱ የሰሜን ኮርያ ጦር በጦርነቱ መሳተፍ ከመጀመሩ በፊት መፍትሄ እንዲበጅለት ጠይቀዋል
8 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮርያ ጦር አባላት በከርስክ ክልል መሰማራታቸውን የአሜሪካ ደህንንት ተቋማት መረጃ አመላክተዋል
ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ የዩክሬን አጋሮች የሰሜን ኮርያ ጦር አባላት አገራቸውን በውጊያ ከመጋፈጣቸው በፊት እርምጃ እንዲወስዱ ጠየቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በሩስያ በስልጠና ላይ እንደሚገኙ ከተረጋገጠ መቆየቱን፤ የዩክሬን የደህንነት ተቋማትም ይህንን መረጃ በተደጋጋሚ ይፋ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም አጋሮቻችን ቆመው ከመመልከት ተላቀው የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ ውስጥ መገኝታቸውን በተመለከተ አንዳች እርምጃ ሊወስዱ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል፡፡
ዘለንስኪ በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጸው ባስተላለፉት መልዕክት ሰሜን ኮርያ ወታደራዊ አቅሟን እያሳደገች ነው፣ የሚሳኤል ሙከራ እና የጦር መሳርያ ምርት አቅሟም ጨምሯል አሁን ደግሞ በዘመናዊ ውግያ ላይ ልምዷን እንድትፈትሽ እድል አግኝታለች ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሰሜን ኮሪያ የመጡት የመጀመሪያዎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዩክሬናውያን አሁንም በውጭ ሀገር በመጣ ጦር የሚፈጸምባቸውን ጥቃት ለመመከት ይገደዳሉ ፤ዓለም ደግም እንደገና ከዳር ሆኖ ይመለከታል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ዘለንስኪ በቪድዮ መልዕክታቸው ዩክሬን ሁሉም የሰሜን ኮርያ ወታደሮች በሩስያ ሰፍረው የሚገኙባቸውን ቦታዎች ለይታ እንደምታውቅ ነገር ግን በሩስያ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል የረጅም ርቀት ሚሳኤል ስለሌላት አሁንም ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገዳለች ብለዋል፡፡
ይህ ሲሆን አሜሪካ ፣ ጀርመን እና ብሪታንያ ቆመው እየተመለከቱ ነው ሲሉ ሀገራቱን በስም ጠርተው ነቀፌታቸውን አሰምተዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው የዩክሬን እና ሩስያን ጦርነት እንዲስፋፋ የማይፈልግ ማንኛውም አካል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ፕሬዝዳንቱ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ባሳለፍነው ሀሙስ ባደረጉት ንግግር በሩስያ 10 ሺህ የሰሜን ኮርያ ወታደሮች መስፈራቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ከነዚህ መካከልም ስምንት ሺህ ያህሉ ባሳለፍነው ነሀሴ ዩክሬን ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመችበት ከርስክ ክልል ውስጥ ተሰማርተዋል ነው ያሉት ፡፡
በትላንትናው እለት ለጉብኝት ሩስያ የገቡት የሰሜን ኮርያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቾ ሶን ሁይ ፒዮንግያንግ ሞስኮ የዩክሬንን ጦርነት እስከምታሸንፍ ድረስ ከጎኗ እንድምትቆም ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡