ትራምፕ ለሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን ተጠያቂ አደረጉ
የሪፐብሊካኑ እጩ ዘለንስኪ ጦርነቱን ማስቆም የሚፈልግ ከሆነ የተወሰኑ የዩክሬን መሬቶችን ለሩሲያ መልቀቅ ሊኖርበት ችላል ብለዋል
ትራምፕ በዘለንስኪ ላይ ካሰሟቸው ነቀፌታዎች ይህኛው ጠንከር ያለ ነው ተብሏል
ትራምፕ ለሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን ተጠያቂ አደረጉ።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና የ2024ቱ ምርጫ የሪፐብሊካን እጩ ዶናልድ ትራምፕ ለሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መጀመር ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ ተጠያቂ እንደሆኑ ተናገሩ፡፡
በምርጫ ቅስቀሳ መድረኮች እና ቃለ መጠይቆች ፕሬዝዳንቱ ላይ ተደጋጋሚ ትችቶችን የሚሰነዝሩት ትራምፕ “የምድራችን ትልቁ የሽያጭ ሰራተኛ” ሲሉ ዘለንስኪን ወርፈው ነበር፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ይህን ያሉት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ እና ምዕራባውያንን በማሳመን ዘለንስኪ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ ማግኝታቸውን ባነሱበት ንግግር ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በዘለንስኪ ላይ ከተሰነዘሩት ትችቶች ጠንካራ እንደሆነ በተወራለት ንግግር “ምንም እንኳን ጦርነቱ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ቢጀመርም ዘለንስኪ ጦርነቱን ማስቆም ባለመቻሉ ብቻ ሳይሆን እንዲጀመር በመርዳት ተጠያቂ ነው” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ትራምፕ የዩክሬኑን መሪ ከሞስኮ ጋር ሰላም መፈለግ ባለመቻላቸው ወቅሰው ዩክሬን የሰላም ስምምነት ለማድረግ የተወሰነ መሬቷን ለሩሲያ አሳልፋ ልትሰጥ እንደምትችል ጠቁመዋል፡፡
ሮይተርስ ይህ የትራምፕ ንግግር በህዳር አምስቱ ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ፖሊሲያቸው ወደ ሩሲያ ሊያደላ እንደሚችል ማሳያ ነው ሲል ዘግቧል፡፡
የዘንድሮው ምርጫ ዴሞክራቶችን ከነጩ ቤት አስወጥቶ ሪፐብሊካንን የሚያስገባ ከሆነ ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ በእጅጉ ሊቀንስ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ይህን ሀሳብ ተቀናቃኛቸው የዴሞክራት እጩ ካማላ ሃሪስም በተደጋጋሚ ሲያንጸባርቁት ከዚህ ቀደም ተስተውለዋል፡፡
“ትራምፕ አምባገነኖችን ለማወገዝ የሚግደረደር ከፑቲንም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያለው ነው” ያሉት ሃሪስ የፕሬዝዳንትነት ቦታውን የሚይዝ ከሆነ ዩክሬን ብቻዋን ልትቆም ትችላለች ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሆኖም የሪፐብሊካኑ እጩ “ይህ ማለት በምርጫው ካሸነፍኩ ዘለንስኪን መደገፍ አቆማለሁ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም የሀገሪቱ ዜጎችች ያሳዝኑኛል ነገር መጀመርያም ቢሆን ከሩሲያ ጋር ጦርነት እንዳይጀመር ማስቆም ነበረበት” ነው ያሉት፡፡
ባሳለፍነው መስከረም ወር ዘለንስኪ “የድል እቅድ” ያሉትን በሩስያ ላይ ተጨማሪ ጫናዎች እንዲደረጉ እና ለዩክሬን የሚደረጉ የጦር ማሳሪያ ድጋፎች የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን በብዛት እንዲያካትት የሚጠይቀውን እቅድ ለአሜሪካ መሪዎች ባቀረቡበት ወቅት ሁለቱንም ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች “ጨዋዎች” ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በምን አይነት መንገድ እንደሆነ ግልጽ ባያደርጉም ፕሬዝዳንት የሚሆኑ ከሆነ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነትን በፍጥነት እንደሚያስቆሙ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተስተውለዋል፡፡