የአህያ ቄራዎች በእንስሳቱ ላይ የህልውና አደጋ መደቀናቸው ተገለጸ
በኢትዮጵያ በቀን 300 አህዮች እንደሚታደረዱ ተገልጿል
የቻይና ኩባንያዎች ከፍተኛ በጀት መድበው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገልጿል
የአህያ ቄራዎች በእንስሳቱ ላይ የህልውና አደጋ መደቀናቸው ተገለጸ።
አህያን ጨምሮ የጋማ ከብቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ የተቋቋመው ዓለም አቀፉ ግብረ ሰናይ ድርጅት ብሩክ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ድርጅቱ እንዳለው በኢትዮጵያ በቻይናዊያን ኩባንያዎች የተቋቋሙት የአህያ ቄራዎች በእንስሳቱ ላይ የህልውና አደጋ ደቅነዋል ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ እና አሰላ ከተሞች የተገነቡት የአህያ ቄራዎች ለአህያ ህልውና ዋነኛ ስጋት ሆኗልም ተብሏል።
ከዓመታት በፊት በቢሾፍቱ የተቋቋመው የአህያ ቄራ በህዝብ ተቃውሞ የተዘጋ ቢሆንም በአሰላ ያለው ግን በቀን እስከ 300 አህዮች እየታረዱበት እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለቻይናዊያን ኩባንያዎች እርዱን እንዲያከናውኑ መፍቀዱን የተቸው ብሩክ ኢትዮጵያ አሁን ባለው የእርድ መጠን ከቀጠለ በ20 ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ አህያዎች ህልውና ለከፍተኛ ስጋት እንደሚጋለጥም አስታውቋል።
እርዱን እያከናወኑ ያሉት የአህያ ቄራዎች ቆዳውን ወደ ቻይና በመላክ ላይ ሲሆኑ የአህያው ቆዳ ለባህላዊ የቆዳ መድሀኒት መስሪያ ይውላል ተብላል።
ቻይና በዓለም ሀገራት በምታካሂዳቸው የአህያ ቆዳ ንግድ በአፍሪካ ፣ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ ሀገራት በአህያ ህልውና ላይ አደጋ ደቅናለች የተባለ ሲሆን በርካታ ሀገራትም የአህያ ቄራዎችን በመዝጋት ላይ ናቸው።