ከሰሜን ኮሪያ መሪ ለቀድሞ ደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የተሰጡ ውሾች በበጀት እጥረት ምክንያት ወደ መካነ እንስሳት ተወሰዱ
ውሾቹ ስማቸው አንገታቸው ላይ ታስሮ ጋዜጠኞችና ሌሎች ጎብኚዎች በመካነ እንስሳቱ ውስጥ ፎቶ ሲያነሱዋቸው ታይተዋል
ጉሚ እና ሶንግጋንግ የተባሉት ውሾቹ “በደቡብ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል የሰላም ምልክት” ተደርገው የሚታዩ ናቸው
በሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለቀድሞ ደቡብ ኮሪያ መሪ የተሰጡ ውሾች በበጀት እጥረት ምክንያት እንደማንኛውም እንስሳ ወደ መካነ እንስሳት መወሰዳቸው ተሰማ።
የሰሜን ኮሪያው መሪ በፈረንጆቹ 2018 የወቅቱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሙን ጄ ኢ ተቀብለው ካነጋገሩ በኋላ ሁለት የሰሜን ኮሪያ ዝርያ ያላቸው ነጭ የፖንግሳን አዳኝ ውሾች በስጦታ ማበርከታቸው ይታወሳል።
ኪም ለደቡብ ኮሪው አቻቸው ውሾች የሰጡበት አጋጣሚ፤ የኪም ሟቹ አባት ኪም ጆንግ ኢል እንደፈረንጆቹ በ2000 ሁለቱ ኮሪያዎች ከክፍፍላቸው በኋላ በተደረገው የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሆኑም በወቅቱ የዓለም ትኩረት የሳበ ነበር።
ጉሚ እና ሶንግጋንግ የተባሉት ሁለቱ ውሾች ደቡብ ኮሪያ ከገቡ በኋላ የቀድሞ መሪ ሙን ስልጣን ላይ አስከነበሩበት ወቅት በደቡብ ኮሪያ ቤተ መንግስት አስፈላጊውን እንክብካቤ ሲደረግላቸው ቆይተዋል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ በቀድሞው ፕሬዝደንት እና በመንግስት መካከል ለምግብ ክፍያ እና ለእንስሳት ህክምና በመክፈል ምክንያት የተፈጠረው አለመግባባት ተከትሎ ሁለቱ ውሾች ወደ ደቡብ ኮሪያ ወደሚገኝ መካነ እንስሳት እንዲዘዋወሩ መደረጉ ተሰምቷል።
በህዳር መጀመሪያ ላይ የሙን ቢሮ መንግስት የውሻ ምግብ እና የእንስሳት ህክምና ወጪዎችን ለመሸፈን ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፕሬዝዳንት የዩን ከሰዋል።
የዮን ቢሮ ግን ሙን የከለከልነው ገንዘብ የለም የገንዘብ ድጋፍ ስለመስጠት ውይይቶች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው ሲል ክሱን ውድቅ አድርጓል።
የመካነ እንስሳት ባለስልጣናት እንዳሉት ጉሚ እና ሶንግጋንግ በደቡብ ምስራቅ ዴጉ ከተማ በሚገኘው የእንስሳት ህክምና ሆስፒታል ጊዜያዊ ቆይታ ካደረጉ በኋላ በደቡባዊ ጓንግጁ ከተማ በአካባቢው ባለስልጣናት ወደሚተዳደረው መካነ አራዊት ተዛውረዋል ብለዋል።
ውሾቹ ሰኞ እለት ስማቸው አንገታቸው ላይ ታስሮ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ጎብኚዎች ፎቶ ሲያነሱዋቸው ታይተዋል።
የጓንጁ ከንቲባ ካንግ ጃጆንግ "ጉሚ እና ሶንግጋንግ በደቡብ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል የሰላም፣ የእርቅ እና የትብብር ምልክቶች ናቸው፤ እንደ የሰላም ዘር መዝራት እንንከባከባቸዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።