የቁም እንስሳት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አጎራባች ሀገራት እንዲወጡ መደረጉ ኢትዮጵያን እየጎዳ ነው ተባለ
ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታርና ግብጽ ከምስራቅ አፍሪካ የቁም እንስሳትና ስጋን በመቀበል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ
ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሃብት በአፍሪካ 1ኛ ብትሆንም የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ በመላክ ሱዳን እና ጁቡቲ ይበልጧታል
የቁም እንስሳት በህገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደ አጎራባች ሀገራት እንደሚወጡ መደረጉ ጉዳት እያስከተለ፤ መሆኑን የግብርና ሚኒሰቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ፤ በድንበር በኩል እንደ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ጁቡቲና ሱዳን የሚደረግ ህገ-ወጥ የቁም እንስሳትን የመላክ ድርጊት ሀገሪቱን ለኪሳራ እያደረጋት ነው ሲሉ ለአል-ዐይን ኒውስ ተናግረዋል።
በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ የሚላኩት የቁም እንስሳት አሁን ላይ ተገቢውን ሂደት ሳያሟሉ የሚላኩ እንደመሆናቸው በተቀባይ ሀገራት በኩል ቅሬታዎች ከመፍጠር ባሻገር ወደ ኢትዮጵያ እስከመመለስ የደረሱበት ሁኔታ እንዳለም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ያለው ድርቅ አብዛኛው የቁም እንስሳት ባሉባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ያጋጠመ በመሆኑ ዘርፉን ኩፉኛ መጉዳቱንም ተናግረዋል።
ከድርቁ ጋር ተያይዞ ያጋጠመውን አደጋ ለማቃለል በተለይም ከውሃ እና መኖ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉትን ድክመቶች በመለየት ሚኒሰቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
አትዮጵያ የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ የምትልከው የጁቡቲን ወደብ በመጠቀም እንደመሆኑ “እንስሳት ተለይተው የሚቆይባቸው ማእከላትን (የኳራንታይን ስፍራዎችን) ተረክበን ወደ ስራ እየገባን ነው”ም ነው ያሉት አቶ ፍቅሩ።
በዘርፉ የሚገኘውን ሀገራዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ በእፋር ክልል የሚገኘው የሚሌ ከዋራንታይን ማእክል አግልጎሎቱን በማሻሻል በቅርቡ በሙሉ አቅሙ ስራ እንደሚጀምርም ጭምር ተናግሯል።
ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሃብት በአንደኝነት ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ሀገር ብትሆንም ወደ ተቀባይ ሀገራት የቁም እንስሳትን በመላክ በኩል ሱዳን እና ጁቡቲ ይብልጧታል።
እንደ አቶ ፍቅሩ ረጋሳ ከሆነ የቁም እንሰሳት በመላክ ሂደት የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት የኢጋድ አባል ሀገራት ከሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ኤስያ ተቀባይ ሀገራት ጋር እየመከሩ መሆኑን አስታውቋል።
በኢጋድ እና የተመድ የምግብ እና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) አማካኝነት የተዘጋጀና በቁም እንስሳት እና ስጋ አቅረቦት ዙርያ የሚመክር 5ኛው የጋራ የመድረክ በአዲስ አበባ በመካሄደድ ላይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መድረኩ በላኪዎችም ሆነ በተቀባይ ሀገራት የሚያገጥሙ መሰረታዊ ችግሮች ላይ በመምከር መፍትሄዎችን ለማመላከት የሚያስችል ነው ብሏል።
ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ግብጽ ከምስራቅ አፍሪካ የቁም እንስሳትን እና ስጋን በመቀበል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ሀገራት ናቸው።