ተመድ አፍጋኒስታንን እና ኢትዮጵያን ጨምሮ እርዳታ ለማዳረስ 41 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገለጸ
አፍጋኒስታን፣ሶሪያ፣የመን፣ኢትዮጵያ እና ሱዳን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሀገራት ናቸው ተብሏል
ተመድ “በኢትዮጵያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 26 ሚልዮን ሰዎች አሉ” ብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍጋኒስታን እና ኢትዮጵያ የሚገኙትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለግጭትና ድህነት ሰለባ የሆኑትን የ183 ሚሊዮን ዜጎች ህይወትን ለማዳን፤ በሚቀጥለው አመት 41 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውና እንዲሰጠው ተማጸነ፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያም ሆነ በሌሎች ምክንያት በ43 ሀገራት የሚኖሩ 45 ሚሊዮን ሰዎች ተርበው “ የወደፊት እጣፈንታቸው አስፈሪ በሚባል ደረጃ ” እንደሚገኝም ተመድ አስታውቋል፡፡
አመታዊ የገንዘብ ፍላጎቶች 17 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብሏል ተመድ።
የተመድ የእርዳታ ሃላፊ ማርቲን ግሪፍትስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የፍላጎቶቹ ገፊ ምክንያቶች ሁላችን የምናውቃቸው ናቸው፤ በሚያሳዝን ሁኔታ ፣ የተራዘሙ ግጭቶችን ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ፣ ያልተሳኩ ኢኮኖሚዎች እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ የምናውቃቸው ምክንያቶች ቢሆኑም፤ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አዲሱ ቀውስ የ COVID-19 ወረርሽኝንም በምክንያትነት ሊነሳ የሚችል ነው" ብሏል፡፡
ማርቲን ግሪፍትስ"ቀጣይ እና አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ቀጣዩ የ2022 ዓመት አስከፊ ሊሆን ይችላል" ሲሉም አስጠንቅቋል፡፡
አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በቀውስ ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙና ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አምስት ዋና ዋና ሀገራት ናቸውም ነው ያሉት ሃላፊው፡፡
ለ27 ዓመታት በዘለቀው የከፋ ድርቅ 24 ሚልዮን የሚሆኑ ዜጎቿ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙባትና በታሊባን የምትመራው አፍጋኒስታን “ፍላጎቷ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ” ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ፤ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ብሏል፡፡
ግሪፍትስ "በዓለም ባንክ ድጋፍ እና በተመድ ሲስተም የገንዘብ ልውውጥ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ እንዲገባ የሚያስችል ተነሳሽነት በፍጥነት ለመመስረት ስራዎችን በማከናወን ላይ ነን" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
"በአፍጋኒስታን ውስጥ የጥሬ ገንዘብ አለመኖር ለማንኛውም አገልግሎት አሰጣጥ ትልቅ እንቅፋት" ሆኖ እንደሚገኝም አስታውሷል፡፡
በኢትዮጵያ ያለውና አንድ አመት ያስቆጠረው ጦርነት አሁን ላይ አድማሱን አስፍቶ ከትግራይ ክልል በተጨማሪ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በመዝለቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል ያለው ተመድ፤ ድርቅ እና የአንበጣ ወረርሺኝ ተጨምሮበት ችግሩ ይበልጥ ተባብሷልም ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ 26 ሚልዮን ዜጎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና 400 ሺ ሰዎች የረሃብ አደጋ እንደተደቀነባቸው ተመድ መግለጹ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሃይሎች ጋር እየተዋጋ ነው ያሉት ግሪፍትስ፤ “ለታፈነች ኢትዮጵያ ምላሽ የመስጠት አቅም መገመት ፈጽሞ አይቻልም” በማለትም የሁኔታውን ክብደት አስረድቷል።