የፀጥታው ም/ቤት በህዳር አፍጋኒስታንን፣ የመንን እና ሶሪያን የተመለከቱ ስብሰባዎች ያደርጋል ተባለ
የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን ማድረጉ ይታወሳል
ምክር ቤቱ በሱዳን እና በማይናማር ሁኔታ ላይም ስብሰባ ሊያደረግ ይችላል ተብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ኅዳር ወር ላይ በአፍጋኒስታን፣ በየመን፣ በሶሪያ እንዲሁም በአጠቃላይ በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ሁኔታ ዙሪያ ስብሰባ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
በተመድ የሜክሲኮ አምባሳደር እና የኅዳር ወር የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሁዋን ራሞን ዴ ላፉንቴ የምክር ቤቱ የአንድ ወር የሥራ ዕቅድ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አምባሳደሩ እንዳሉት በአፍጋኒስታን፣ በየመን እና በሶሪያ ምን እየተካሄደ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ በኅዳር ወር ስብሰባዎች እንደሚኖሩት አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በቦሲኒያና ሄርዜጎቪኒያ፣ በሶማሊያ፣ በኢራቅ፣ በሊቢያና በጥቅሉ በመካከለኛው ምሰራቅ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስብሰባዎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ በዚህም መሰረት በአፍጋኒስታን ጉዳይ ላይ በፈረንጆቹ ኅዳር 17 ላይ ስብሰባ ይኖራል ተብሏል፡፡
በፈረንጆቹ ኅዳር 9 የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አንድሪያስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር የሚመሩትና በዓለም አቀፍ የጸጥታ ችግሮች ላይ ያተኮረ ክፍት ክርክር እንደሚኖርም ተገልጿል፡፡
የጥቅምት ወር የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤትን በሊቀመንበር የመራችው ኬንያ የነበረች ሲሆን የኅዳር ወር ሊቀመንበር ደግሞ ሜክሲኮ ሆናለች፡፡ የጥቅምት እና የኅዳር የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሊቀመንበሮቹ ኬንያ እና ሜክሲኮ የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባላት ናቸው፡፡
የፀጥታው ም/ቤት በህዳር ወር በሱዳን እና በማይናማር ሁኔታ ላይም ስብሰባ ሊያደረግ እንደሚችል ተገልጿል፡፡የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን ማድረጉ ይታወሳል፡፡