ለክፉ ቀን መሸሸጊያ በሚል የተገነቡ ቤቶች ዋጋ እየናረ ነው ተባለ
ሩሲያ ከአንድ ወር በፊት ኦሬሽኒክ የተሰኘውን ሚሳኤል ከተኮሰች በኋላ ቤቶቹን ለመግዛት የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ ተገልጿል
የኑክሌር ጦርነትን ለማምለጥ ተብለው የተገነቡ ቤቶች ዋጋ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 137 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል ተብሏል
ለክፉ ቀን መሸሸጊያ በሚል የተገነቡ ቤቶች ዋጋ እየናረ ነው ተባለ።
የኑክሌር አረራ የታጠቁ ሀገራት ወደ ጦርነት ይገባሉ በሚል ስጋት ምክንያት ሰዎች የተሻለ ደህንነት መፈለጋቸውን ቀጥለዋል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም የተሻለ ሰላም አግኝታ የነበረ ቢሆንም ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ግን በተለይም የኑክሌር አረር የታጠቁ ሀገራት ግንኙነት እየተባባሰ መጥቷል።
ለአብነትም አሜሪካ እና ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ቁጥጥር ስምምነትን ያቋረጡ ሲሆን ይህም ሀገራትን ወደ ፉክክር እና ግጭት እንዳያስገባቸው ተሰግቷል።
በነዚህ ምክንያትም ሰዎች ለክፉ ቀን መሸሸጊያ የሚሆኑ መጠለያዎችን እየገነቡ መሆኑን ኤፒ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የክፉ ጊዜ መጠለያ ቤቶችን የሚገዙ እና የሚገነቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
ለአብነትም ባለፈው ዓመት ብቻ ለክፉ ቀን መሸሸጊያ በሚል 137 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ አሀዝ በቀጣዮቹ ዓመታት ወደ 170 ሚሊዮን ዶላር ሊያድግ ይችላል ተብሏል።
የኮሮና ቫይረስ፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና በሌሎች ሀገራት ያሉ ግጭቶች ለክፉ ቀን መሸሸጊያ ቤቶች ዋጋ መጨመር ምክንያት ሆነዋል ተብሏል።
ሩሲያ ከአንድ ወር በፊት ወደ ዩክሬን ኤሬሽኒክ የተሰኘውን የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል ከተኮሰች በኋላ የቤቶቹ ዋጋ ጭማሪ እንዳሳየም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
እንደ ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነ ሰዎች የክፉ ቀን መሸሸጊያ የሚገነቡት ከኑክሌር ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ለማምለጥ ሳይሆን ከመጀመሪያዎቹ ፍንዳታዎች እና ጨረር ጥቃት ለማለጥ በሚል ነው።
የሀገራት ኑክሌር አረር በጀት 91 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህም በአውዳሚ መሳሪያዎች የታገዘ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት እንዲነሳ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አስከትሏል።
የኑክሌር ጦር ተመራማሪዎች በበኩላቸው የሰዎችን ስጋት ለማስቆም ብቸኛው እና አስተማማኙ መፍትሄ የኑክሌር ጦርነት ስጋትን ማስቆም እንደሆነ ተናግረዋል።