ዩክሬን የኑክሌር መሳሪያ የምትታጠቅ ከሆነ ሩሲያ በእጇ ያሉትን ሁሉንም መሳሪያዎች ትጠቀማለች ሲሉ ፑቲን አስጠነቀቁ
ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ለዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልታስታጥቅ ትችላለች የሚል ዘገባ ወጥቶ ነበር
ፑቲን ሩሲያ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እየተከታተለች ነው ብለዋል
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያ የምትታጠቅ ከሆነ ሩሲያ በእጇ ያሉትን ሁሉንም አይነት መሳሪያዎች ተጠቅማ ዩክሬንን እንደምታጠቃ ፑቲን በትናንትናው እለት አስጠንቅቀዋል።
የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት በስም ያልጠቀሳቸውን ምዕራባውያን ባለስልጣናት ጠቅሶ እንደዘገበው ጆ ባይደን ከኃይት ሀውስ ከመውጣታቸው በፊት ለዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሊሰጧት ይችላሉ።
"እየተዋጋን ያለችው ሀገር የኑክሌር ጦር መሳሪያ የምትታጠቅ ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን? ይህ ከሆነ በሩሲያ ያሉ አውዳሚ መሳሪያዎችን ሁሉ እንጠቀማለን።ይህ እንዲሆን አንፈቅድም፤ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን እየተከታተልን ነው" ሲሉ ፑቲን በካዛኪስታን አስታና በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ፑቲን እንዳሉት ለዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያ "በይፋ አሳልፎ የሚሰጥ አካል ካለ፣ ሁሉንም 'የነን-ፕሮላይፈሬሽን'(የጦር መሳሪያን ምርት መገደብ) ስምምነትን ይጥሳሉ ማለት ነው።"
ፑቲን አክለውም ዩክሬን ብክለት ሊፈጥር የሚችል'ደርቲ ቦምብ" ልትሰራ ትችል ይሆናል፤ ነገርግን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልታመርት አችልም ብለዋል።
ሊዚህም ቢሆን ሩሲያ ተመጣጣኝ ምላሽ ትሰጣለች ብለዋል ፑቲን።
ዩክሬን ሶቬት ህብረት ከፈራረሰች በኋላ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የወረሰች ቢሆንም በ1994 በዳፔስት በተደረገው ስምምነት ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ የደህንነት ዋስትና ሲሰጧት መሳሪያዎቹን ላለመጠቀም ተስማምታለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ይህ ስምምነት ሀገራቸው ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል ሲሉ በተጋጋሚ ቅሬታ እያሰሙ ናቸው።