አሜሪካ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለዩክሬን የመመለስ እቅድ እንደሌላት ገለጸች
ኪቭ ሶቬት ህብረት በ1991 ከፈራረሰች በኋላ የኑክሌር ጦር መሳሪያ መውረስ የቻለች ቢሆንም በ1994ቱ የቡዳፔስት ስምምነት አሳልፋ ሰጥቻለች
ባይደን ስልጣን ከመልቀቃቸው በፊት ለዩክሬን ኑክሌር ጦር መሳሪያ ሊያስታጥቁ ይችላሉ የሚል ሪፖርት ወጥቶ ነበር
አሜሪካ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለዩክሬን የመመለስ እቅድ እንደሌላት ገለጸች።
አሜሪካ ዩክሬን ከሶቬት ህብረት መፈራረስ በኋላ ያጣችውን የኑክሌር ጦር መሳሪያ የመመለስ እቅድ እንደሌላት የኃይት ሀውስ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ባይደን ስልጣን ከመልቀቃቸው በፊት ለዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሊሰጡ ይችላሉ ስለሚለው የባለፈው ወር የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሪፖርት ተጠይቀው ነው ሱሊቫን ይህን አስተያየት የሰጡት።
"በእቅደ አልተያዘም።አሁን እያደረግን ያለነው ዩክሬን የመደበኛ ውጊያ አቅሟን አሳድጋ ሩሲያን እንድትከላከል እንጅ ኑክሌር ለማስታጠቅ አይደለም" ማለታቸውን ሮይተርስ ኤቢሲ ኒውስን ጠቅሶ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት ይህ ሀሳብ "ፍጹም እብደት" መሆኑን እና ሩሲያ ወደ ዩክሬን ጦር ያዘመተችውም እንዲህ አይነት ክስተቶችን ለመከላከል መሆኑን ገልጻለች።
ኪቭ ሶቬት ህብረት በ1991 ከፈራረሰች በኋላ የኑክሌር ጦር መሳሪያ መውረስ የቻለች ቢሆንም በ1994ቱ የቡዳፔስ ስምምነት አሳልፋ ሰጥቻለች። ዩክሬን የኑክሌር ጦር መሳሪያውን አሳልፋ ለመስጠት ስትስማማ፣ በምላሹ ሩሲያ፣ ዩክሬን እና ብሪታንያ የደህንነት ዋስትና ስጥተዋት ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ መፍቀዳቸው እና ይህን ተከትሎ ሩሲያ ኦርሽኒክ የተባለ የመካከለኛ ርቀት ሚሳይል ወደ ዩክሬን ማስወንጨፏ ጦርነት ጡዘት ላይ ደርሷል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ያቀረባቸው የንግግር ቅድመ ሁኔታዎች የተራራቁ በመሆናቸው ምክንያት ጦርነቱን ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም።
ዩክሬን የሩሲያን ጦር ከግዛቷ መውጣትን በቅደመ ሁኔታነት ስታስቀምጥ፣ ሩሲያ ደግሞ ጦርነቱ የሚቆመው በከፊል የያዘቻቸውን ዩክሬን ግዛቶች ይዛ ስትቆይ መሆኑን ገልጻለች።