በጀርመን ሙኒክ መኪና በሰዎች ላይ በመንዳት በተፈጸመ ጥቃት 30 ሰዎች ቆሰሉ
የ24 አመት አፋጋኒስታናዊ ጥገኝነት ጠያቂ ጥቃቱን ማድረሱና በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/14/273-111431-54b41790-e9f6-11ef-bcac-87abe8b9d53e_700x400.jpg)
ጥቃቱ የተፈጸመው የዩክሬን ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በሚሳተፉበት የሙኒክ የደህንነት ጉባኤ ዋዜማ ነው
በጀርመን ሙኒክ ከተማ መኪና በሰዎች ላይ በፍጥነት በመንዳት በተፈጸመ ጥቃት በጥቂቱ 30 ሰዎች ቆሰሉ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ጀርመን ከምታካሂደው የፌደራል ምርጫ ከአንድ ሳምንት በፊት ነው።
የሙኒክ ፖሊስ አሽከርካሪው ፋርሃድ ኤን የተባለ የ24 አመት አፍጋኒስታናዊ ጥገኝነት ጠያቂ መሆኑንና በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል።
የትራንስፖርት ሰራተኞች ማህበር የተቃውሞ ሰልፍ ሲያካሂዱ ነው ግለሰቡ ተሽከርካሪውን በፍጥነት በመንዳት ጉዳት ያደረሰው።
መራሄ መንግስት ኦላሽ ሾልዝ ወጣቱ "መቀጣትና ወደ ሀገሩ መመለስ አለበት" ብለዋል።
ሙኒክ በተሽከርካሪ የሚፈጸም ጥቃት ያስተናገደችው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ እና የአሜሪካውን ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚሳተፉበት የሙኒክ የደህንነት ጉባኤ ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።
በጀርመን እየተደጋገመ የመጣው በተሽከርካሪ የሚፈጸም ጥቃት እና የስደተኞች ጉዳይ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ዋነኛ ጉዳይ ይሆናል ተብሏል።
የጀርመን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ህጻናትን ጨምሮ 30 ሰዎች የቆሰሉበትን ጥቃት የፈጸመው አፍጋኒስታናዊ በፈረንጆቹ 2016 ነው ወደ ጀርመን የገባው።
ግለሰቡ ያቀረበው የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ በ2020 ወደ ሀገሩ መመለስ ቢኖርበትም የአፍጋኒስታን የጸጥታ ሁኔታ ተገዶ ከጀርመን እንዳይወጣ ማድረጉንም ዘገባው አክሏል።
ከሁለት ወራት በፊት በማግደቡርግ ከተማ የገና ገበያ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት ስድስት ሰዎች መሞታቸውና ከ300 በላይ መቁሰላቸውን ቢቢሲ አስታውሷል።
ከሶስት ሳምንት በፊት አሻፈንቡርግ ከተማ ህጻን እና የ41 አመት ጎልማሳ ፓርክ ውስጥ በስለት ተወግተው መገደላቸው የሚታወስ ነው።
ሙኒክን ባካተተው የባቫሪያ ግዛት በንጹሃን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተደጋገሙ መሆኑና ጥቃት አድራሾቹ ስደተኞች ናቸው መባሉ የኦላፍ ሾልዝ መንግስት ጠንከር ያለ የስደተኞች ፖሊሲ እንዲያወጣ ጫና እያሳደረበት ነው።
በቀጣዩ ምርጫ የሚሳተፈው የኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመኒ (ኤፍዲ) ፓርቲም ስደተኞችን በብዛት ወደ ሀገራቸው እንደሚመልስ እየቀሰቀሰ ነው።
የኦላፍ ሹልዝ ፓርቲም ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ስደተኞችን ወደ አፍጋኒስታን የመመለሱ ስራ በነሃሴ ወር መጀመሩንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።