ጀርመን የቤት ውስጥ ጥቃት ለሚፈጽምባቸው ወንዶች መጠለያ ማዘጋጀት ጀመረች
በ"ወንዶች መጠለያዎቹ" በሴቶች አካላዊ፣ ወሲባዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት የደረሰባቸው ወንዶች ብሶታቸውን የሚተነፍሱበት እድል ተመቻችቶላቸዋል
ላይፕዚሽ፣ ባቫሪያ እና ሳክሶኒ ግዛቶች የጀመሩትን እንቅስቃሴ ሃምቡርግም ተቀብላዋለች ተብሏል
በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አብዛኛውን ጊዜ ከሴቶች ጋር የተያያዙ ይምሰሉ እንጂ ወንዶችም የችግሩ ሰለባዎች ናቸው።
በትዳር እና የፍቅር አጋራችን ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት ተፈጽሞብናል፤ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃት ደርሶብናል የሚሉ ወንዶች እየተበራከቱ ነው።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ወንዶች የቤት ውስጥ ጥቃቱን ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ማድረግ እንደፈሪ ያስቆጥረናል፤ በማህበረሰቡም ዘንድ አጉል ስም ያሰጠናል በሚል ህመማቸውን በውስጣቸው ይይዛሉ።
የጀርመን ግዛቶችም ይህ በወንዶች ላይ የሚፈጸም የቤት ውስጥ ጥቃት እየጨመረ መሄድ አሳሳቢ ነው በሚል ለመፍትሄው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ረጂም ጊዜ የሚያሳልፉት ለምንድን ነው?
"ሌማን ኢቪ" የተሰኘ ተቋም በላይፕዚሽ ከተማ "የወንዶች መጠለያ" የሚል ስያሜ የሰጠውን ፕሮጀክት አስተዋውቋል።
መጠለያው በሴቶች አካላዊ፣ ስነልቦናዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል የሚሉ ወንዶች ለተወሰነ ጊዜ እፎይታ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
"ተጠቂዎቹ" የደረሰባቸውን የቤት ውስጥ ጥቃት ያለምንም ፍርሃት ለሌሎች እንዲያጋሩ እድል ይሰጣቸዋል። ጥቃቱ ያስከተለባቸው አዕምሯዊ ጉዳት እንዲሽርም በባለሙያዎች ተከታታይ ስነልቦናዊ ምክር ይለገሳቸዋል።
የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ወንዶች ወደ ቀደመ አካላዊና ስነልቦናዊ ጤናቸው እንዲመለሱ የሚረዳው "የወንዶች መጠለያ"፥ በመሰል ጥቃት ውስጥ ያለፉ አባቶችና ህጻናት ወንዶችን ለመቀበልም ዝግጁ መሆኑን ታግ 24 የተሰኘው የጀርመን ድረገጽ አስነብቧል።
ወንዶች በቤት ውስጥ የሚደርስባቸው ጥቃት እንደ ሴቶቹ ሁሉ እኩል ትኩረት እንዲያገኝ የጥቃቱ ሰላባ ወንዶች ዝምታቸውን መስበር አለባቸው ተብሏል።
ከላይፕዚሽ ባሻገር ባቫሪያ፣ ሳክሶኒ እና ሮርዝ ሪን ዌስትፋሊያ ግዛቶች የቤት ውስጥ ጥቃት የደረሰባቸውን ወንዶች ለመደገፍ ተመሳሳይ ፕሮጀክት ነድፈው ወደ ስራ ገብተዋል።
ሃምቡርግ ከተማም ለወንዶች የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች የመጀመሪያውን "የወንዶች መጠለያ" ለመክፈት ማቀዷን ሃምቡርግ አቤንድብላት ጋዜጣ ዘግቧል።