በበሽር አላሳድ ደጋፊዎችና በአዲሱ የሶሪያ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል በተከፈተ ውግያ 70 ሰዎች ተገደሉ
በሀገሪቷ የባህር ዳርቻ ከተሞች የተፈጠረው ግጭት ከአሳድ መወገድ በኋላ የተካሄደ ከፍተኛ ውጊያ ነው ተብሏል

ይህን ተከትሎም አዲሱ መንግስት በሁለት የሶሪያ ከተሞች ላይ የሰዓት እላፊ አውጇል
በቀድሞው የሶሪያ መሪ በሽር አላሳድ ታማኞች እና በአዲሱ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል በተካሄደ ከፍተኛ ውግያ ከ70 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡
በታህሳስ ወር የ50 አመታቱን የአሳድ አስተዳደር ከስልጣን ያስነሳው አዲሱ የሶሪያ መንግስት ሀገሪቷን ለማረጋጋት እና መንግስታዊ ቁመናን ለመላበስ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ሆኖም የበሽር አላሳድ መንግሰት ደጋፊዎች በብዛት ከሚገኙባቸው አካባቢዎች አልፎ አልፎ በሚያጋጥሙት ግጭቶች እየተፈተነ ይገኛል፡፡
የትላንቱ ውግያ የተከሰተው ላታኪያ በተባለችው የባህር ዳርቻ ከተማ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች ለደህንነት ስራ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ከታጣቂዎች በተፈጸማባቸው ድንገተኛ ጥቃት መሆኑ ታውቋል፡፡
የሶሪያ የባህር ዳርቻ ከተሞች የበሽር አላሳድ ቤተሰቦች እና የቀድሞዎ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የአልዋቲ ሙስሊሞች መኖሪያ ናቸው ፡፡
ሐሙስ እለት ማምሻ ላይ፣ መቀመጫውን በሶሪያ ያደረገው ስቴፕ የዜና ወኪል ይዞት በወጣው መረጃ የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች ወደ 70 የሚጠጉ የቀድሞ የአገዛዙ ተዋጊዎችን ሲገድሉ ከ25 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በጃብሌ እና አካባቢው መያዛቸውን ዘግቧል።
በሌላ በኩል በጦርነቱ ወቅት የአማጽያን ጠንካራ ይዞታ በነበረባቸው አሊፖ እና ሆምስ አካባቢዎች ማንነታቸው ካልታወቁ ታጣቂዎች ጋር የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ውግያ ከፍተው እንደፈነበር እና ከፍተኛ የጦር መሳሪ ድምጽ መሰማቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሶሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሀሰን አብዱልጋኒ በላታኪያ እና ታርቶውስ ለሚዋጉት ለአሳድ ታማኝ ወታደሮች በመንግስት ሚዲያ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
"በሺዎች የሚቆጠሩት መሳሪያቸውን አስረክበው ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስን መርጠዋል፣ አንዳንዶች ደግሞ ገዳዮችንና ወንጀለኞችን በመጠበቅ መሞትን የመረጡ አሉ ምርጫው ግልፅ ነው መሳሪያችሁን ፍቱ ወይም የማይቀረውን እጣ ፈንታችሁን ትጋፈጣላችሁ" ብለዋል።
የአህመድ አልሻራ መንግስት አሳድ ደጋፊዎች ከሚገኙበት የባህር ዳርቻ ከተሞች ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከድሩዝ ሀይሎች ጋር ውጊያ ውስጥ ገብቶ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሶሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአለም አቀፉ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ቁጥጥር ድርጅት በአሳድ ስር የተመረቱትን ቀሪ የኬሚካል መሳሪያ ክምችቶችን ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሯል።
የአሳድ መንግስት ለ14 አመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት የኬሚካል ጦር መሳሪያ መጠቀሙን ቢክድም የማህበረሰብ አንቂዎች ግን በደርዘን የሚቆጠሩ የኬሚካል ጥቃቶችን ፈጽሟል ሲሉ ከሰዋል።