አል ሻራ የሶሪያ የሽግግር ፕሬዝዳንት መሆኑን በማወጅ ስልጣኑን አጠናከረ
የሶሪያ ህገመንግስት እንዲታገድና ጊዜያዊ የህግ አውጪ ምክርቤት እንዲዋቀርም አሳድን ከስልጣን ለማንሳት በተካሄደው ዘመቻ የተሳተፉ ወታደራዊ መሪዎች ወስነዋል
በአሳድ የስልጣን ዘመን የተመረጠው ፓርላማም መበተኑ ተገልጿል
በሽር አል አሳድን ከስልጣን ያነሳው አማጺ ቡድን መሪ አህመድ አል ሻራ የሶሪያ የሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንት መሆኑን አወጀ።
ከሁለት ወር በፊት አሳድን ከስልጣን ለማስወገድ በተካሄደው ፈጣን ዘመቻ የተሳተፉ ወታደራዊ አዛዦች ምክክር ካደረጉ በኋላ አል ሻራ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት እንዲሆን መወሰናቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የቀድሞው የአልቃይዳ ክንፍ ሃያት ታህሪር አል ሻም አዛዡ ሶሪያ ከአሳድ መወገድ በኋላ ህገመንግስት አሻሽላ ምርጫ ለማካሄድ በጥቂቱ አራት አመታት ያስፈልጋል ማለቱ ይታወሳል።
አል ሻራ ለምን ያህል ጊዜ በፕሬዝዳንትነት እንደሚቆይ ባይገለጽም ህገመንግስቱን አግዶ ጊዜያዊ የህግ አውጪ ምክርቤት እንዲያዋቅር በወታደራዊ አዛዦቹ ስልጣን ተሰጥቶታል ተብሏል።
ከሹመቱ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠው አህመድ አል ሻራ ቀዳሚው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚታየውን ክፍተት "በህጋዊ መንገድ መሙላት" ነው ብሏል።
ለ13 አመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችውን ሀገር ሰላም ለማረጋገጥና በቀልን ለማስወገድ የሽግግር ጊዜ ፍትህ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ጠቅሷል።
የሽግግር ፕሬዝዳንቱ የሶሪያን ወታደራዊ እና የደህንነት ተቋማት ዳግም የማደራጀት ስራ እንደሚሰራና ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለማጥበብ ሁሉን አካታች ብሄራዊ ምክክር እንደሚካሄድ አብራርቷል።
የትናንቱ ውሳኔ አዲስ ህገመንግስት እስኪጸድቅ ድረስ የሚዋቀረው የህግ አውጪ ምክርቤት መቼ ወደ ስራ እንደሚገባና ዝርዝር ጉዳዮችን አልጠቀሰም።
ባለፈው አመት በበሽር አል አሳድ የስልጣን ዘመን የተመረጠው ፓርላማ እንዲሁም የአሳድ ባዝ ፓርቲና እና የደህንነት ተቋማቱ እንዲፈርሱ መወሰኑ ይታወሳል።
በ13 አመቱ ጦርነት ከሶሪያ ጦር ጋር ሲዋጉ የቆዩ አማጺ ቡድኖችም በመከላከያ ሰራዊቱ ስር እንዲሆኑ ውሳኔ ላይ መደረሱ አይዘነጋም።
የሶሪያን አዲስ አስተዳደር እንደምትደግፍ ያስታወቀችው ኳታር የአል ሻራ ፕሬዝዳንት ሆኖ መሾም "ሶሪያን ዳግም ለመገንባትና በፓርቲዎች መካከል አንድነት ለመፍጠር ያግዛል" ብላለች።
ሹመቱ አል ሻራ ሶሪያን ወክለው በአለማቀፍ መድረኮች እንዲገኙ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሳለች።
የሽግግር ፕሬዝዳንቱ ደማስቆ በአሳድ አገዛዝ የተጣሉባትን ማዕቀቦች የማስነሳት፣ የጎሳ፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነቶችን የማቀራረብና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የማድረግ ብሎም የፈራረሰችውን ሀገር ዳግም ግንባታ የማስጀመር ከባድ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።