በርካታ የአሜሪካ ጀቶች ከ24 ሰዓታት በኋላ ካቡል እንደሚገቡ ይጠበቃል
በአውሮፕላን ማረፊያ መግቢያ በሮች ማለፍ የሚችሉት አሜሪካውያን፣ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውና የኔቶ አባል ሀገራት ዜጎች ብቻ ናቸው ተብሏል
እያንዳንዳቸው 400 ሰዎችን የሚጭኑት ጀቶች በ24 ሰዓት ውስጥ ሃሚድ ካርዛይ አውሮፕላን ማረፊያእንደሚደርሱ ይጠበቃል
ከአፍጋኒስታን ዜጎችን ለማስወጣት ዛሬም በርካታ የአሜሪካ ጀቶች በካቡል ሃሚድ ካርዛይ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚደርሱ ተገለጸ።
አሁን ላይ በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል በሚገኘው አውሮፕላን 20 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደሚገኙ የዘገበው ሲኤንኤን የአሜሪካ አውሮፕላኖች በ24 ሰዓት ውስጥ ካቡል እንደሚገቡ ዘግቧል።
እያንዳንዳቸው 400 ሰዎችን እንደሚጭኑ የሚጠበቁት ጀቶች በ24 ሰዓት ውስጥ አፍጋኒስታን ይገባሉ ነው የተባለው።
ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ ከሀገሪቱ የሚወጡ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ አሁን ባለው ወቅታዊ መረጃ ብቻ በሃሚድ ካርዛይ አውሮፕላን ማረፊያ 20 ሺህ ሰዎች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ምንም እንኳን ዋሸንግተን አውሮፕላኖችን ብትልክም ወደ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገቡ ሰዎች ላይ ለውጥ ማድረጓ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በአውሮፕላን ማረፊያ መግቢያ በሮች ማለፍ የሚችሉት አሜሪካውያን፣ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው እና የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) አባል ሀገራት ዜጎች ብቻ እንደሆኑ አሜሪካ አስታውቃለች።
ሲኤንኤን እንደዘገበው ከአፍጋኒስታን ሰዎችን ለማስወጣት አሜሪካ ልዩ የቪዛ ፕሮግራም የጀመረች ቢሆንም አሁን ላይ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዲገቡ አላደረጋቸውም ነው የተባለው።
ምንም እንኳን ወደ አውሮፕላን ማረፊያ መግቢያ በሮች ማለፍ የሚችሉት አሜሪካውያን፣ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) አባል ሀገራት ዜጎች ብቻ እንደሆኑ አሜሪካ ብትገልጽም፤ ሰነድ የሌላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍጋናውያን አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እንዳሉ ተገልጿል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ከአፍጋኒስታን ሰዎችን በማስወጣቱ ሂደት ሀገሪቱን ከተቆጣጠረው ታሊባን እስካሁን እንቅፋት እንዳልገጠማቸው ቢገልጹም የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ግን አሜሪካውያን እየተደበደቡ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።