ጆ ባይደን፤ ከአፍጋኒስታን ሰዎችን በማስወጣቱ ታሊባን እንቅፋት አለመሆኑን ገለጹ
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው አሜሪካውያን እየተደበደቡ እንደሆነ ተናግረዋል
አፍጋናውያን አሁንም ሀገራቸውን ለቀው መውጣታቸውን ቀጥለዋል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ከአፍጋኒስታን ሰዎችን በማስወጣቱ ሂደት ሀገሪቱን ከተቆጣጠረው ታሊባን እስካሁን እንቅፋት እንዳልገጠማቸው ቢገልጹም የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ግን አሜሪካውያን እየተደበደቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
ታሊባን ካቡልን በፈረንጆቹ ነሐሴ 15 ቀን ከተቆጣጠረ በኋላ ሀገራቸውን ለቀው የሚወጡ አፍጋናውያን ቁጥር መጨመሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ሂደት ምንም አሜሪካ ዜጋ ችግር እንዳልገጠመው ገልጸዋል።
የፔንታጎን ኃላፊ ሎይድ ኦስቲን ግን አሜሪካውያን ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ሲገቡ ካቡልን በያዘው የታሊባን ኃይሎች እየተደበደቡ መሆኑን ገልጸዋል። የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ንግግር መቃረን መነጋገሪያ እንደሆነም እየተገለጸ ነው።
ፕሬዝዳንት ባይደን ታሊባን አፍጋኒስታንን በአጭር ጊዜ መቆጣጠሩን ተከትሎ ከመላው ዓለም ወቀሳ እየቀረበባቸው ሲሆን አሜሪካ በሀገሮች ላይ የመግባት ተልዕኮዎች እንዳልተሳኩ ማሳያ እየተደረጉ ናቸው።
ከሰሞኑ በካቡል በሚገኘው ሃሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሀገር ለመውጣት ሲደረግ የነበረው ግርግር አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ እየተገለጸም ይገኛል።
አሁን ላይ የሃሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሀገራቸውን ለቀው ለመውጣት በሚፈልጉ ሰዎች መጨናነቁን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
አሜሪካ እስካሁን 13ሺ ሰዎችን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷን የገለጹት ጆ ባይደን ከአፍጋኒስታን የማስወጣቱ ኦፕሬሽን በታሪክ ትልቁ እና አስቸጋሪው እንደሆነ ገልጸዋል።
እረፍታቸውን አቋርጠው ወደ ኋይት ሃውስ የተመለሱት ባይደን ከአሜሪካዊ ዜጎች ባለፈም ከአሜሪካ ጋር ሲሰሩ የነበሩ ከ50 እስከ 65 ሺህ የሚደርሱ አፍጋኒስታናውያንንም ለማስወጣት ተመሳሳይ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ታሊባን የአሜሪካን ፓስፖርት የያዘ ማንኛውም ሰው ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እንዲገባ እየፈቀደ መሆኑን በመጥቀስ የአሜሪካ ወታደሮችን ወደ ካቡል መላክ አስፈላጊ እንደማይሆን ገልጸዋል።