ታሊባን ለአፍጋኒስታን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ምህረት ማድረጉን አስታወቀ
ሁሉም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል
የታሊባን ቡድን ባሳለፍነው እሁድ የሀገሪቱን ዋና ከተማ ካቡልን በቁጥጥር ስር አውሏል
የአፍጋስታን ዋና ከተማን ካቡልን ተቆጣጠረው የታሊባን ቡድን ለቀድሞ አፍጋኒስታን መንግስት የስራ አመራሮች ምህረት ማድረጉን አስታወቀ።
ለሁሉም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ምህረት አድርጌያለሁ ያለው ታሊባን፤ ሁሉም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች ወደ ስራቸው እንዲመለሱም ጥሪ አቅርቧል።
ታሊባን አዲስ ያሳለፈው ውሳኔ ቡድኑ በትናትናው እለት በአፍጋኒስታን ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ሰብአዊ ድጋፍ ድርጅቶች እና የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ቃል መግባን ተከትሎ እንደሆነም ታውቋል።
የአሜሪካ እና የሰሜን አትላቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ከአፍጋኒስታን ለቆ መውጣት ከጀመረበት ዕለት ጀምሮ ታሊባን የአፍጋኒስታንን በርካታ ግዛቶች መቆጣጠሩ ይታወቃል።
ባለፉት 3 ወራ በርካታ የሀገሪቱን ግዛቶች በቁጥጥር ስር ያዋለው ታሊባን ባሳለፍነው እሁድ የሀገሪቱን ዋና ከተማ ካቡልን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል።
በሁኔታው የተደናገጡ መንግስት ሰራተኞች ቢሯቸውን ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በርካታ ሲቪሊያን የሚሆነውን ነገር በስጋት ውስጥ ሆነው እየተጠባበቁ ነበር።
የታሊባን ታጣቂዎች ካቡልን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ ሀገሪቱን ለቀው መውጣታቸውም ይታወቃል።
ካቡል በታሊባን እጅ መውደቋን ተከትሎ በርካታ አፍጋናውያንና የሌሎች ሃገራት ዜጎች በካቡል ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ለቀው ለመውጣት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ትንቅንቅ ብዙዎችን አስገርሟል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትናትናው እለት በሰጡት መግለጫ ሀገሪቱ በታሊባን እጅ ለማደቋ የአፍጋኒስታን አመራሮችን ወቅሰዋል።