እርዳታ ሲጠባበቁ የነበሩ ከ100 በላይ ፍልስጤማውያን ተገደሉ
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር የእስራኤል ወታደሮች ድጋፍ ሲጠባበቁ በነበሩ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ገልጿል
የእስራኤል ጦር በበኩሉ “አስደንጋጭ” ነው ያለውን ክስተት እየመረመርኩ ነው ብሏል
በሰሜናዊ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ ለመቀበል የሚጠባበቁ 104 ፍልስጤማውያን ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ።
ከ750 በላይ ፍልስጤማውያን መቁሰላቸውንም የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያሳያል።
ሚኒስቴሩ የእስራኤል ወታደሮች እርዳታ ወደሚጠባበቁ ንጹሃን ተኩስ በመክፈት ግድያ ፈጽመዋል የሚል ወቀሳ አቅርቧል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አሽራፍ አል ቁድራ ክስተቱን “የእስራኤል የዘር ማጥፋት” ሙከራ ነው ያሉት ሲሆን፥ ክፉኛ የቆሰሉት ፍልስጤማውያን ወደ አል ሺፋ ሆስፒታል እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ “አስደንጋጭ” ነው ያለውን ክስተት እየመረመረ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፥ ፍልስጤማውያኑ እርዳታ በጫኑት ተሽከርካሪዎች ተገጭተው ህይወታቸው ሳያልፍ እንደማይቀር ገልጿል።
በጋዛ የሚገኙ ጋዜጠኞች ግን የእስራኤል ታንኮች እርዳታ ለመቀበል ወደተሰባሰቡት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ሲተኩሱ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በጦርነቱ ህይወታቸው የተቀጠፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ30 ሺህ መሻገሩን በገለጸ በስአታት ልዩነት የተፈጠረውን አሳዛኝ ክስተት የሚያሳዩ ምስሎችም እየወጡ ነው።
የመንግስታቱ ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ከ576 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ከባድ የምግብ እጥረት ውስጥ የሚገኙ ናቸው ማለቱ ይታወሳል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ ግጭቱ ባለመቆሙና የተራቡ ፍልስጤማውያን እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን እየዘረፉና አሽከርካሪዎቹ ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው በሚል በሰሜናዊ ጋዛ የእርዳታ ስርጭት ማቆሙን ማሳወቁ አይዘነጋም።