የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሽታየህ ስልጣን ለቀቁ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት አሜሪካ የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት መሀሙድ አባስ አስተዳደሩን እንዲያስተካክለው ጫና እያደረገች ባለችበት ወቅት ነው
ሽታየህ ለካቢኔ አባላት በሰጡት መግለጫ ቀጣዩ ምዕራፍ በጋዛ ያለውን እውነታ ከግምት ማስገባት የሚጠይቅ ነው ብለዋል
የፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሽታየህ ስልጣን ለቀቁ።
የፍልስጤሙ ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሽታየህ እስራኤል በጋዛ በሀማስ ላይ የምታደርገውን ጦርነት ተከትሎ ስለሚኖረው የፖለቲካ መዋቅር በፍልስጤማውያን መካከል መግባባት እንዲፈጠር ለማድረግ በዛሬው እለት ስልጣን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት አሜሪካ የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት መሀሙድ አባስ አስተዳደሩን እንዲያስተካክለው ጫና እያደረገች ባለችበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚነስትሩ ሰው እስከሚተካቸው ድረስ ባለአደራ ሆነው እንዲቀጥሉ በፕሬዝደንት መሀሙድ አባስ ሊጠየቁ ይችላሉ ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2019 ስልጣን የያዙት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሽታየህ ለካቢኔ አባላት በሰጡት መግለጫ ቀጣዩ ምዕራፍ በጋዛ ያለውን እውነታ ከግምት ማስገባት የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
ሽታየህ አዲሱ ምዕራፍ "በጋዛ ሰርጥ ያለውን እውነታ ከግምት ያስገባ አዲስ መንግስት እና ፖለቲካዊ አወቃቀር፣ የብሔራዊ አንድነት ንግግሮች እና በፍልስጤማውያን መካከል መግባባት ያስፈልጋል" ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም አሁን ላይ ፍልስጤምን እያስተዳደረ ያለው አስተዳደር ስልጣኑንን በጠቅላላ የፍልስጤም መሬት ላይ ማስፋት እንደሚያስፈልግ ሽታየህ ተናግረዋል።
የፍልስጤም አስተዳደር በጊዜያዊው የኦስሎ የሰላም ስምምነት ነበር ከ30 አመታት በፊት የተቋቋመው።
አስተዳደሩ በተወሰነ የዌስትባንክ ክፍል እና በጋዛ የማስተዳደር ስልጣን የነበረው ቢሆንም በፈረንጆቹ 2007 ከሀማስ ጋር በነበረው የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በጋዛ ያለውን ስልጣን አጥቷል።
የአንድነት መንግስት ለመመስረት ጥረት እያደረጉ ያሉት ፍልስጤምን እያስተዳደረ ያለው ፋታህ እና ሀማስ በመጭው ረቡዕ በሩሲያ ሞስኮ ሊገናኙ ነው ተብሏል።