የአለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜናዊ ጋዛ የእርዳታ አቅርቦቱን አቋረጠ
ሃማስ የድርጅቱን ውሳኔ ከ750 ሺህ በላይ በሚሆኑ ፍልስጤማውያን ላይ የተላለፈ “የሞት ቅጣት” ነው ብሎታል
አሜሪካ የጸጥታው ምክርቤት የጋዛ ተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብን ለሶስተኛ ጊዜ ተቃውማለች
የአለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜናዊ ጋዛ የሚያቀርበውን እርዳታ ማቋረጡን አስታወቀ።
ድርጅቱ በአካባቢው ያለው “ከባድ ቀውስ” እርዳታ ለማቅረብ አስቻይ አይደለም በሚል ነው ውሳኔውን ያሳለፈው።
ውሳኔው በደመነፍስ የተወሰነ ሳይሆን እርዳታው ለሚገባቸው ሰዎች መድረሱን ማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ነው ያለው የአለም ምግብ ፕሮግራም፥ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን ገልጿል።
ከሶስት ሳምንት በፊት በተሽከርካሪዎች ላይ ተኩስ በመከፈቱ እርዳታውን ማቋረጡን በማውሳትም፥ ከሰሞኑም የተራቡ ሰዎች ተሰብስበው እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ በመተኮስና ሾፌሮቹን በመደብደብ ለመዝረፍ ሞክረዋል ብሏል።
ድርጅቱ የሰራተኞቹ ደህንነት ሲጠበቅና እርዳታ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ሲቆም እርዳታውን በፍጥነት ማድረስ እንደሚጀምር ነው ያስታወቀው።
ሃማስ የድርጅቱን ውሳኔ በሰሜናዊ ጋዛ በሚኖሩ ከ750 ሺህ በላይ በሚሆኑ ፍልስጤማውያን ላይ የተላለፈ “የሞት ቅጣት” ነው ብሎታል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም ውሳኔን በፍጥነት እንዲቀለብስ ያሳሰበው ቡድኑ፥ ይህ ካልሆነ ግን በረሃብ ለሚያልቀው ህዝብ የመንግስታቱ ድርጅት ተጠያቂ ይሆናል ማለቱን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በሰሜናዊ ጋዛ ከሚኖሩ ስድስት ህጻናት አንዱ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር ውስጥ ይገኛሉ ብሏል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በተደጋጋሚ እያሳለፈው ያለው የምግብ ድጋፍ አቅርቦት የማቋረጥ ውሳኔም በተለይ ረሃብ የመቋቋም አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ህጻናትን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል ነው የተባለው።
በዚህ ፈታኝ ወቅት አልጀሪያ ለጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው የጋዛ ተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳብ በአሜሪካ ውድቅ ተደርጎ ሳይጸድቅ ቀርቷል።
የእስራኤል አጋሯ አሜሪካ በጋዛ “ጊዜያዊ ተኩስ አቁም” እንጂ ሁለቱንም ወገን ተጠያቂ የሚያደርግ ዘላቂ የተኩስ አቁም መደረግ አይገባውም በሚል ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ የተቃወመችው ለሶስተኛ ጊዜ ነው።