ህንድ ከታዳሽ ሃይል 500 ጊጋዋይት ሃይል ለማመንጨት እየሰራች መሆኑ የሚደነቅ ነው - አል ጀበር
የአለም የዘላቂነት ጉባኤ በኒውደልሂ ሲካሄድ ነው የኮፕ28 ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጀበር የህንድን የታዳሽ ሃይል ልማት ያደነቁት
አል ጀበር በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ላከናወኗቸው ስራዎች በህንድ የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል
የኮፕ28 ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጀበር ህንድ በሰባት አመት ውስጥ ከታዳሽ ሃይል 500 ጊጋዋይት ሃይል ለማመንጨት የያዘችውን እቅድ አደነቁ።
የአለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጀበር፥ በታዳሽ ሃይል ልማት በስፋት እየሰራች ያለችው አረብ ኤምሬትስ ከህንድ ጋር በትብብር መስራት ትፈልጋለች ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ መልዕክተኛው በኒውደልሂ እየተካሄደ ባለው የአለም የዘላቂነት ጉባኤ ንግግር አድርገዋል።
- የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት መሀመድ ቢን ዛይድ 2023ን "የዘላቂነት ዓመት" በሚል አወጁ
- የኮፕ 28 ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጃበር ማን ናቸው?
አል ጃበር በንግግራቸው ኤምሬትስ በፈረንጆቹ 2015 የተፈረመውን የፓሪስ ስምምነት በማክበር የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እየሰራች መሆኑን ነው ያነሱት።
የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት አፈጻጸም አሁንም ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን የጠቀሱት የኮፕ28 ፕሬዝዳንቱ፥ አቡዳቢ የምታስተናግደው ጉባኤ አለምን እየፈተነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመግታት ከወትሮው አካሄድ ለየት ይተዋወቅበታል ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚደረገው ድርድር፥ የታዳሽ ሃይል ልማት በሶስት እጥፍ የመጨመር፣ ሰላማዊ የኒዩክሌር የሃይል ምንጮች የማስፋፋት እና ካርቦን የሚያምቁ ቴክኖሎጂዎች በስፋት የማስተዋወቅ እድል ይፈጥር ዘንድም የሚመሩት ቡድን እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ድርድሩ ከ800 ሚሊየን በላይ ከኤሌክትሪክ ሃይል ጋር ያልተዋወቁ ህዝቦች የሚገኙባቸውን ሀገራት ያልዘነጋ እንዲሆንም በትኩረት እንደሚሰራ ነው አል ጀበር ያነሱት።
ለአየር መበከል አንድ ሶስተኛ ድርሻ ያለውን የምግብ ስርአት የማስያዙ ጉዳይም በኮፕ28 ጉባኤ ይመከርበታል ብለዋል።
የምድራችን ነዋሪዎች ንጹህ ውሃ እንዲያገኙና የምግብ ስርአታቸውም ከብክለት የጸዳ እንዲሆን ከባለድርሻዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶች እንደሚካሄድም ነው ፕሬዝዳንቱ ያብራሩት።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በእጥፍ እንዲያድግ እና የፋይናንስ ተቋማት በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ ተሳትፏቸው እንዲጎለብት እየተሰራ መሆኑንም በመጥቀስ።
የብዝሃ ህይወትና ስርአትምድር ጥበቃ ስራዎችን በተመለከተም ከህንድ የሚቀሰሙ በርካታ ልምዶች መኖራቸውን በማንሳት፥ ተፈጥሮን መጠበቅ የሁላችንም ግዴታ ነው ብለዋል።
ለታዳሽ ሃይል ልማትና በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተጎዱ ለሚገኙ ሀገራት ድጋፍ በትሪሊየን ዶላር የሚቆጠር ሃብት ማሰባሰብ እንደሚጠበቅ ያብራሩት አል ጀበር፥ የአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ሴክተር በዚህ ረገድ ተሳትፎው እንዲጠናከር የሚመሩት ቡድን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጀበር፥ ውጤታማ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ ለበርካቶች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።
ከኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ ትልቁን የታዳሽ ሃይል ልማት አቢዮት በመክፈት ለበርካታ ዜጎችና የቢዝነስ ተቋማት ስራ መፍጠር እንችላለንም ነው ያሉት።
የኮፕ28 ፕሬዝዳንቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በሚከናወኑ ስራዎች ማንም ከዳር ሆኖ ማየት የለበትም፤ ሁሉንም ወደ ድርድር ጠረጼዛ በማምጣት በትብብር ችግሮችን ለመቅረፍ ይሰራል ሲሉም አብራርተዋል።
የኮፕ28 ቢሮም በቀጣዮቹ ወራት ከሲቪል ድርጅቶች፣ ከግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች፣ ከመንግስት አመራሮች፣ ከሴቶች እና ወጣቶች ጋር አካታች የውይይት መድረኮችን በመፍጠር እንደሚሰራ ተገልጿል።
የኮፕ28 ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሱልጣን ቢን አህመድ አል ጀበር በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለከወኑት ድንቅ ስራ ከህንዱ የኢነርጂ እና አካባቢ ጥበቃ የጥናት ተቋም (TERI) የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
አል ጀበር ይህን ሽልማት የወሰዱ የመጀመሪያው ግለሰብ ናቸው ተብሏል።