ሰሜን ኮሪያ ሁለት ባለስቲክ ሚሳይሎችን ወደ ምስራቅ ባህር መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታወቀ
ሚሳይሎቹን የተኮሰችው በተለምዶ የጃፓን ባህር ተብሎ ወደ ሚጠራው ስፍራ ነው ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ በዚህ አመት ብቻ ከ60 በላይ የባላስቲክ ሚሳይሎችን መተኮሷ መረጃዎች ያመለክታሉ
ሰሜን ኮሪያ ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ ምስራቅ ባህር መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታወቀ፡፡
ዮንሃፕ የዜና አገልግሎት የደቡብ ኮሪያ ጦርን ጠቅሶ እንደዘገበው ፒዮንጊያንግ ሚሳኤሎቹን የተኮሰችው በተለምዶ የጃፓን ባህር ተብሎ ወደ ሚጠራው ስፍራ መሆኑን ሲጂቲዜን ዘግቧል፡፡
በፒዮንጊያንግ ተደጋጋሚ ትንኮሳ የተማረሩት የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ ጥምር ጦር ወታደራዊ አዛዦች በሰሜን ኮሪያ በኩል ሊቃጣ የሚችለውን አደጋ ለመመከት አስፈላጊውን ወታደራዊ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
"ወታደሮቻችን (የደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ) በቅርበት በመተባበር ሙሉ ዝግጁነት አቋማቸውን እየጠበቁ ናቸው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ ሁለቱም ሚሳይሎች ከጃፓን ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና ውጭ ማረፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር እጅግ የላቀ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏን ጨምሮ በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ያለውን ውጥረት እየተባበሰ መጥቷል፡፡
በተለይም አንድ ቀን ጥቃት ይደርስብኛል በሚል ጃፓን በቅርቡ ይፋ ያደረገችውና ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ ነው የተባለ የወታደራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ሰነድ፤ ሰሜን ኮሪያን እጅጉን ያስደነገጠ ዜና ሆኗል፡፡
በጃፓን እቅድ የተደናገጡት የፒዮንጊያንግ ባለስልጣናት የቶኪዮ አዲሱ የደህንነት ስትራቴጂ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ፒዮንጊያንግ በተግባር ለማሳየት ዝግጁ መሆናቸው በቅርቡ ዝተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይህም በምስራቅ እስያ የጸጥታ አካባቢ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እቅድ በመሆኑ ቀጠናው ወደለየለት ቀውስ እንዳይወስደው ተሰግቷል፡፡ሰሜን ኮሪያ በዚህ በዚህ አመት ብቻ ከ60 በላይ የባላስቲክ ሚሳኤሎችን መተኮሷ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡