ሰሜን ኮሪያ ለስለላ ሳተላይት ባለቤትነት መቃረቧ ተገለጸ
በትናንትናው እለት ወደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሚሳኤል ያስወነጨፍኩት የሳተላይት ምስሎች የማንሳት አቅሜን ለማየት ነውም ብላለች
ፒዮንግያንግ የስለላ ሳተላይቶችን የማበልጸግ ስራዋ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀችው
ሰሜን ኮሪያ ለስለላ ሳተላይት ባለቤትነት መቃረቧ ተገለጸ።
ሰሜን ኮሪያ የሰለላ ሳተላይቷን የመጨረሻ ሙከራ ማድረጓ እየተነገረ ነው።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ውኪል እንደዘገበው ሙከራው የተደረገው በትናንትናው እለት ነው።
በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ሶሃይ በተባለ የሳተላይት ማስወንጨፊያ ማዕከል “የስለላ ሳተላይት” የያዘች ሮኬት ወደ ደቡብ ኮሪያ ተልካለች ነው ያለው ዘገባው።
ሳተላይቷ በርካታ ካሜራዎች፣ ምስል አስተላላፊ እና ተቀባይ እንዲሁም የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች የተገጠሙላት ሳተላይት በ500 ኪሎሜትር ከፍታ ተልዕኮዋን መፈጸሟንም ኬ ሲ ኤን ኤ አስነብቧል።
ወደ ደቡብ ኮሪያ በሮኬት የተወነጨፈችው ሳተላይት የሀገሪቱን የአየር ላይ ምስሎች የማንሳት አቅም የመመዘን አላማ እንደነበራት ተነስቷል።
ሳተላይቷ የደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል እና በአቅራቢያዋ የምትገኘው ኢቺዮን ከተማን አንስታ መላኳም ለፒዮንግያንግ ደስታን ፈጥሯል።
የመጨረሻ ሙከራውን በማድረግ ላይ የምትገኘው የስለላ ሳተላይት በሚያዚያ ወር 2023 ሙሉ በሙሉ ተጠናቃ ወደ ስራ ትገባለች ተብሏል።
ይህም ሀገሪቱ ቁልፍ ወታደራዊ መረጃዎችን እንድታገኝ በማድረግ በዋሽንግተንና በአጋሯ ሴኡል የሚካሄዱ ወታደራዊ ልምምዶችን ጨምሮ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን መመልከት ያስችላታል።
ሰሜን ኮሪያ ትናንት ሁለት መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን እንጂ የስለላ ሳተላይቷን ስለመሞከሯ አልገለጸችም ነበር።
ዛሬ ግን የሳተላይት ምስሎችን በመልቀቅ ለደቡብ ኮሪያ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ሰዳለች።
ሴኡልም ባወጣቸው መግለጫ ፒዮንግያንግ ጸብ አጫሪ ድርጊቷን እንድታቆም በማሳሰብ ከአሜሪካ እና ጃፓን ጋር በመሆን እርምጃ እወስዳለሁ ስትል ዝታለች።
ወታደራዊ በጀቷን በእጥፍ ያሳደገችው ጃፓንም የሰሜን ኮሪያን እንቅስቃሴ መመከት የሚያስችል አዲስ ብሄራዊ የደህንነት ስትራቴጂ ይፋ አድርጋለች።
ሰሜን ኮሪያን ከቻይና እና ሩስያ አስከትላ ብሄራዊ የደህንነት ስጋቴ ናት ያለችው ቶኪዮ ስለ ስለላ ሳተላይቱ እስካሁን አስተያየት ባትሰጥም የቶኪዮ የሳተላይት ምስል እስኪለቀቀ የምትጠብቅ አትመስልም።
በዚህ አመት ከ60 በላይ የሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ የጎርቤቶቿንም ሆነ የአሜሪካን ማሳሰቢያ ወደ ጎን ብላ ራሷን በጦር ማደርጀቷን ቀጥላለች።
በማዕቀብ የተንኮታኮተው ኢኮኖሚዋ ግን ሚሊየኖችን ከረሃብ መታደግ አልቻለም።