ሰሜን ኮሪያ 2 የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ አደረገች
የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራው በቶክዮ ኦሎምፒክ እና በባይደን አስተዳር ላይ ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው- ጃፓን
የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራው ዛሬ ጠዋት የተደረገ ሲሆን ከ420 እስከ 430 ኪሎ ሜትር ርቀት ተወንጭፈዋል
በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ባህር አቅራቢያ ላይ ሁለት የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጓ ተነግሯል።
ሙከራውን ተከትሎም የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በስጡት አስተያየት፤ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራው በቶክዮ ኦሎምፒክ ላይ ውጥረት ለመፍጠር ያለመ ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንዲሁም ሙከራው በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ አዲስ ፖሊሲ እያዘጋጀ ባለው የባይደን አስተዳደር ላይ ጫና ለመፍጠር በማለም የተካሄደ ነው ማለታቸውም ተነግሯል።
የአሜሪካ ጦር ኢንዶ ፓሲፊክ ኮማንድ በበኩሉ፥ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን እና ከአጋሮቹ ጋርም እየመከረበት እንደሆነ አስታውቋል።
የደቡብ ኮሪያ ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት በበኩሉ፥ የሰሜን ኮሪያ አዲስ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ እንዳሳሰበው አስታውቋል።
የሚሳኤል ሙከራውን አስመልክቶ የጃፓን የድንበር ጠባቂዎች የሰሜን ኮሪያ የባላስቲክ ሙከራ ዛሬ ጠዋት ላይ መደረጉን አስታውቀዋል።
የሚሳኤል ሙከራዎቹ በተከታታይ መደረጋቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ጠዋት 1 ሰዓት ላይ ተተኩሶ 420 ኪሎ ሜትር መወንጨፉን፤ ሁለተኛውም ከ20 ደቂቃ በኋላ እንደተተኮሰ እና 430 ኪሎ ሜትር ርቀት መወንጨፉን ገልጸዋል።
ሁለቱም ሚሳኤሎች አጭር ርቀት ተወንጫፊ መሆናቸውንም የጃፓን የድንበር ጠባቂዎች አስታውቀዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደምም ወደ ጃፓን ባህር የሚሳኤል ሙከራ ማድረጓ የሚታወስ ሲሆን፥ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊና ኒኩሌር አረር ተሸካሚ የሆኑት ሚሳኤሎቹ አሜሪካ ድረስ መወንጨፍ የሚችሉ መሆኑም በወቅቱ ተነግሯል።