ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ለማምረት የሚያስችላትን ኬሚካል ማበልጸግ ሳትጀምር አልቀረችም ተባለ
ፕሉቶኒዬም ልክ እንደ ዩራኒዬም ሁሉ ኒውክሌርን ለማምረት ከሚያስችሉ ወሳኝ ሁለት ግብዓቶች መካከል አንዱ ነው
ፒዮንግያንግ ዮንግባዮን በተሰኘው ዋና ኒውክሌር ማብለያ ጣቢያዋ ፕሉቶኒዬም የተሰኘ ኬሚካልን እያበለጸገች ነው ተብሏል
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት የሚያስችላትን ፕሉቶኒዬም የተሰኘ ኬሚካል ማበልጸግ ሳትጀምር አልቀረችም ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
ፕሉቶኒዬም ልክ እንደ ዩራኒዬም ሁሉ ኒውክሌርን ለማምረት ከሚያስችሉ ወሳኝ ሁለት ግብዓቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
የድርጅቱ የአቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ አካል (IAEA) የ5 ሜጋ ዋት አቅም ያለውና ዮንግባዮን የሚገኘው ዋና ኒውክሌር ማብለያ ጣቢያ ስራ ጀምሯል ሲል በዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ከ2018 ታህሳስ እስካሳለፍነው ሃምሌ ድረስ ፒዮንግያንግ ኬሚካል ማበልጸጓን አቁማ ነበር ያለው ተቆጣጣሪው አሁን ግን ስራ መጀመሯን የሚያሳዩ ምልክቶችን ተመለክቻለሁ ሲል ገልጿል፡፡
ዮንግባዮን፤ ለሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሃ ግብር “የደም ስር ነው” የሚባልለት የጥናትና ምርምር ቦታ ነው፡፡
IAEA ባለሙያዎቹ ከፒዮንግያንግ ከተባረሩበት እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ተደራሽነት የለውም፡፡ ሂደቶችን በሳታላይት ከመከታተል እና ምስሎችን ከመተንተን ያለፈ ገብቶ ሊያረጋግጥ የሚችልበት መንገድም የለም፡፡
ሆኖም አሁናዊ ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ ምርት ግብዓት የሚሆኑ ኬሚካሎችን ማበልጸግ መጀመሯ፤ ልክ ከአሁን ቀደም ታደርግ እንደነበረው ሁሉ “ወደ ጦር መሳሪያዎች ሙከራዋ ትመለስ ይሆን?” የሚል ስጋትን በተቋሙ ባለሙያዎች ዘንድ አጭሯል፡፡
ፒዮንግያንግ ለመጨረሻ ጊዜ በ2017 ነበር የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ያረገችው፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን፤ ሃገራቸው የማዕቀብ እፎይታ የምታገኝ ከሆነ ፕሮግራሙን ለማቆም ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በ2019 ተነጋግረው እንደነበር ይታወሳል፡፡