የሰሜን ኮሪያ መረጃ ጠላፊዎች ለኑክሌር መሳሪያ የሚውል ከ 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ መስረቃቸው ተገለጸ
ሀገሪቱ በጠላፊዎቿ የምታገኘውን ገንዘብ እንደ ተጨማሪ የገቢ አማራጭ እንደምታይ ባለሙያዎች ጠቁመዋል
ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ በኑክሌር ዘርፍ በ2020 በትብብር ሲሰሩ እንደነበር የተመድ ሪፖርት አስታውቋል
የኑክሌር መሳሪያ ንጥረ ነገር የማብላላት ስራቸውን እንዲገቱ በሚል የተለያዩ ማዕቀቦች የተጣሉባቸው ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ ፣ እ.አ.አ. በ2020 በረዥም ርቀት ሚሳይል የማበልጸግ ስራ በትብብር ሲሰሩ እንደነበር የተባበሩት መንግስታት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በበተባበሩት መንግስታት ገለልተኛ የተባለ ለባለሙያዎች ቡድን የተዘጋጀ ዓመታዊ ሪፖርት ትናንት ሰኞ የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ለፀጥታው ም/ቤት ቀርቧል፡፡
ምንም እንኳን ቴህራን ባትቀበልም ፣ ሀገሪቱ ከ ፒዮንግያንግ ጋር በ2020 የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይልን በማበልጸግ ረገድ በጋራ ስትሰራ እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የኢራን የኑክሌር መርሀ ግብር፡ እ.ኤ.አ. 2019-ኤፒ
በ2020 ሁለቱ ሀገራት ዳግም በጀመሩት ትብብር በርካታ ለስራው የሚያገለግሉ መረጃዎችን እና ቁሶችን እንደተለዋወጡ ነው በሪፖርቱ የተጠቆመው፡፡
ፒዮንግያንግ የተባበሩት መንግስታትን ድንጋጌዎች በመጣስ በ2020 የኑክሌር እና የባለስቲክ ሚሳይል ስራዋን አጠናክራ እንደቀጠለችም ተገልጿል፡፡ የተመድ ሪፖርት እንደጠቆመው ለኑክሌር እና ለባለስቲክ ሚሳይል መርሀ ግብር ክፍያ ለማዋል ፣ በዚሁ ዓመት የሀገሪቱ የመረጃ ጠላፊዎች ቡድን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከተለያዩ የውጭ ተቋማት ሰርቀዋል፡፡ ጠላፊዎቹ ከ2019 መጨረሻ እስከ 2020 ድረስ ከተለያዩ ተቋማት 316.4 ሚሊዮን ዶላር መመዝበራቸው ተጠቁሟል፡፡
የድንጋይ ከሰል ዋነኛ የገቢ ምንጯ የሆነው ሰሜን ኮሪያ ፣ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በ2020 ኤክስፖርቷ በመቆሙ የመረጃ ጠላፊዎቿን በመጠቀም ከተለያዩ የዓለም ተቋማት የምትዘርፈውን ገንዘብ እንደ አማራጭ የገቢ ምንጭ ስለመጠቀሟ ባለሙያዎች እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ይህ ድርጊቷ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ነው ባለሙያዎች የገለጹት፡፡
ሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳይል መሰረተ ልማቷን ያሳደገች ሲሆን ለሚሳይል ስራው የሚውሉ ቁሳቁሶችን እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት አድርጋለችም ነው የተባለው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ሙሉ ሪፖርቱን መች ይፋ እንደሚያደርግ አልተገለጸም፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በ2018 ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ሁለት ጊዜ ተገናኝተው የተወያዩ ቢሆንም ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ባህር ሰርጓጅ ሚሳይል ሰርታ ማጠናቀቋን በወታደራዊ ትርዒት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡