ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ከዚህ አለም በሞት ተለዩ
ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና በኮቪድ 19 ሳቢያ ዛሬ ማለዳ በ85 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል
ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ለ41 ዓመታት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁም ነገር ያበቁ እናት ናቸው።
ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና በCOVID-19 ተይዘው በጳውሎስ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆየተው ዛሬ ማለዳ በ85 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡
በ1972 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮ ድርቅ ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁለት ህፃናትን በመያዝ አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበርን መመስረታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።
አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ በመባል የሚታወቁት ክብርትዶ/ር አበበች ባለፉት 41 በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁነገር ያበቁ ሲሆን፤ በተለይዩ ድህነት ቅነሳ ፐሮግራሞች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሰጥተዋል።
በመሆኑም በተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ታላላቅ ሽልማቶችና እውቅናዎችን እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ በሰብአዊነት አግኝተዋል።
ክብርትዶ/ር አበበች ጐበና በ1928 ዓ.ም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ በግራር ጃርሶ ወረዳ በቶርበን አሼ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ሸበል አቦ በተባለች የገጠር መንደር ነው የተወለዱት።
በወቅቱ በነበረው ባህልና ልማድ ገና የ11 ዓመት ልጅ እንዳሉ ትዳር ለመያዝ የተገደዱ ቢሆንም፤ ቀረበላቸውን የጋብቻ ጥያቄ በብቸኝነት በመቃወም ወደ አዲስ አበባ ገቡ።
በአዲስ አበባ ስራን ሳይንቁ ከግለሰቦች ቤት ከማገልገል እስከ ምርት ክፍል ኃላፊነት ማገልገላቸውን የአበበች ጎበና የህጻናት ክብካቤና ልማት ማህበር መረጃ ያመለክታል።