የዲአር ኮንጎ ብሔራዊ ጦር እና በአካባቢው ያለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር 45 አማጺያንን ገደሉ
አማጺያኑን የተገደሉት በምስራቃዊ ኮንጎ በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ ነው
ዲሞክራሲ ሀይሎች ህብረት በመባል የሚታወቀው ይህ አማጺ ቡድን በኡጋንዳ ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጇል
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ(ዲአር ኮንጎ) ብሔራዊ ጦር እና በአካባቢው ያለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር 45 አማጺያንን መግደላቸውን አስታውቀዋል፡፡
በውድ ማዕድናት የበለጸገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሄራዊ ጦር እና በአገሪቱ የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ጦር ዲሞክራሲ ሀይሎች ህብረት ወይም ኤዲኤፍ በመባል የሚታወቀውን አማጺ ቡድን ወታደሮችን እንደገደለ ገልጿል።
ይህ አማጺ ቡድን በፈረንጆቹ 1990 መጀመሪያ ዓመት አንስቶ በኡጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀስ ሲሆን በኡጋንዳ ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጇል።
አማጺ ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሃላፊነት በመውሰድ ይታወቃል።የዚህን አማጺ ቡድን ጥቃት ለመመከትም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሄራዊ ጦር እና በሀገሪቱ የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ጦር በቅንጅት በወሰዱት እርምጃ 45 አባላቱ እንደገደሉ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
በአማጺ ቡድኑ ላይ የተወሰደው እርምጃ የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት ለማስጠበቅ እንደሆነ የኮንጎ መከላከያ ኮማንደር ብርጋዴር ጀነራል ሲልቬይን ኢኬንጌ ተናግረዋል።