የዲአር ኮንጎ ልዑካን በሕዳሴው ግድብ ድርድር ዙሪያ ከዶ/ር ስለሺ በቀለ ጋር ተወያዩ
የግድቡን ጉዳይ ዓለማቀፋዊ ለማድረግ የወሰኑት ሱዳን እና ግብፅ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል
ኢትዮጵያ በድርድሩ የኮንጎን አመራር በጉጉት እንደምትጠብቅ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚደንት ፌሊክስ ሺሲኬዲ የተወከሉ ልዑካን ከስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) እና ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ሁለቱ አካላት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታና የሦስትዮሽ ድርድር ጉዳይ ላይ ነው የተወያዩት፡፡
ሚንስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትና መፍትሄ ላይ ጽኑ አቋም እንዳላት ለልዑኩ አባላት አረጋግጠዋል፡፡ በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በተካሄደው ውይይት ወቅት ፣
ኢትዮጵያ በድርድሩ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን አመራር በጉጉት እንደምትጠብቅም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው ፣ ኢትዮጵያ በሶስትዮሽ ድርድሩ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኗንም ነው ሚኒስትሩ ለኮንጎው ፕሬዝደንት ልዑካን የገለጹት፡፡
በቀጣይነት በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ይቀጥላል ተብሎ የሚጠበቀውን ድርድር የምትመራው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ልዑካን ከዚህ ቀደም ወደ ግብፅ እና ሱዳንም አቅንተው ከሀገራቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ካይሮ እና ካርቱም ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረትም በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ አቋም መያዛቸውን ለልዑካኑ ከመግለጻቸውም ባለፈ ተከታታይ መግለጫዎችን ሰጥተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ የትብብር ስምምነትም እሁድ እለት ተፈራርመዋል፡፡ ይህ ስምምነት በዋናነት ኢትዮጵያን ለማስጠንቀቅ እና ለማስፈራራት ያለመ እንደሆነ በብዙዎች ታምኗል፡፡ ሱዳን በማንኛውም ጊዜ ለምታቀርበው ወታደራዊ ድጋፍ ግብፅ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን የግብፁ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከስምምነቱ በኋላ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ካለው ውስብስብ ውስጣዊ ፈተናዋ በተጨማሪ በሕዳሴው ጉዳይ ከግብፅ እና ከሱዳን እንዲሁም በድንበር ጉዳይ ደግሞ ከሱዳን ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ ፣ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ ምንም አደራዳሪ እንደማትፈልግ በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
የዲአር ኮንጎ ልዑካን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናትንም እንደሚያናግሩ ይጠበቃል፡፡ ይህን ተከትሎ የሦስቱን ሀገራት ጥቅል ሀሳብ ለአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የሚያቀርቡ ሲሆን ቀጣይ የድርድሩ አካሔድም ከልዑካኑ ሪፖርት ባኋላ ሊታወቅ ይችላል፡፡