በቤልጂዬሞች ተወስዶ የነበረው የነጻነት ታጋዩ የወርቅ ጥርስ ከሰሞኑ ለቤተሰቦቹ መመለሱ ይታወሳል
የኮንጎ የነጻነት ታጋይ ፓትሪስ ሉሙምባ ስርዓት ቀብር ከ61 ዓመት በኋላ ተፈጸመ፡፡
ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በቤልጂየም ቅኝ ግዛት ዘመን ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንደኛዋ ነች፡፡
ሀገሩን ነጻ ለማውጣት በርካቶችን በማደራጀት እና የኮንጎ ነጻ አውጪ በመባል የሚታወቀውፓትሪስ ሉሙምባ በቤልጂየም ጦር ተይዞ በአሰቃቂ መንገድ ተገድሏል፡፡
ሉሙምባ ዲ.አር ኮንጎን ነጻ ካወጣ በኋላ የመጀመሪያው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ አገልግሏል፡፡
ሆኖም ሰኔ 1960 ዘረኝነትን በመቃወም ያደረገው ንግግር በወቅቱ ቅኝ ገዢነቷን ባጣችው ቤልጂዬም ጥርስ ውስጥ እንዲገባና እንዲገደል አድርጎታል፡፡ ቤልጂዬም ሉሙምባን መግደል ብቻም ሳይሆን ሰውነቱ በአሲድ እንዲሟሟ በማድረግ ጭምር ነበር እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ የገደለችው፡፡ ይህም አስከሬኑን እንኳነረ እንዳይገኝ አድርጓል፡፡
በአሲዱ ያልሟሟው የሉሙምባ ብቸኛ የሰውነት ክፍል ሰው ሰራሽ የወርቅ ጥርሱ ብቻ ነበር፡፡ እሱንም ቅኝ ገዢዎቹ ወስደውት ነበር፡፡ ሆኖም አሁን ከሰሞኑ ለሉሙምባ ቤተሰቦች ተመልሷል፡፡
የፓትሪስ ሉሙምባ ስርዓተ ቀብርም ከ61 ዓመታት በኋላ በዲ.አር ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ተፈጽሟል፡፡
ቤልጂየም በቅኝ ግዛት ዘመኗ በኮንጎ በፈጸመቻቸው ጉዳቶች ምክንያት እስከ 10 ሚሊዮን የሀገሪቱ ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቤልጂየም ለዚህ ድርጊቷ ባሳለፍነው ሳምንት ከብራስልስ ኪንሺሳ ድረስ በመምጣት በስራዋ ማዘኗን እና መጸጸቷን በመግለጽ ይቅርታ መጠየቋ ይታወሳል፡፡