ዲሞክራቲክ ኮንጎ የአማጺያን መሪዎችን ለጠቆመኝ አምስት ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች
የኮንጎ ወንዝ ጥምረት የሚባለው የአማጺ ቡድን ስብስብ በምስራቅ ኮንጎ የማዕድን ማውጫዎችን እየተቆጣጠሩ ናቸው

አሜሪካ አማጺያኑን ለመደምሰስ ካገዘች የማዕድን ጥቅም እንደምታገኝ ቃል ተገብቶላታል
ዲሞክራቲክ ኮንጎ የአማጺያን መሪዎችን ለጠቆመኝ አምስት ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች፡፡
በዓለማችን እጅግ ተፈላጊ እና ውድ ማዕድናት የሚገኙባት ዲሞክራቲክ ኮንጎ የትጥቅ ትግል ባነሱ በአማጺን እየተፈተነች ትገኛለች፡፡
አማጺ ቡድኖቹ በተለይም በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ከተሞችን እና የማዕድናት ማውጫ ስፍራዎችን እየተቆጣጠሩ መጥተዋል፡፡
ጎረቤት ሀገር የሆነችው ሩዋንዳ አማጺያኑን ትደግፋለች የሚል ክስ ከኬንሻሳ እየተነሳባት ሲሆን ኪጋሊም የቀረቡባትን ክስ ውድቅ አድርጋለች፡፡
ይሁንና የመንግስታቱ ድርጅት ባለሙያዎች ባሳለፍነው ዓመት ባወጡት ሪፖርት አራት ሺህ የሩዋንዳ ወታደሮች ኤም23 የተሰኘውን አማጺ ቡድንን ተቀላቅለው እየደገፉ ናቸው፡፡
አማጺ ቡድኖቹ በቀርቡ ቡካቩ እና ጎማ የተሰኙ ከተሞችን የተቆጣጠሩ ሲሆን ዓላማቸው በትጥቅ ትግል አማካኝነት የሀገሪቱን መንግስት የመጣል ውጥን እንዳላቸው በይፋ ተናግረዋል፡፡
በምርጫ ስልጣን የተቆጣጠረው የፕሬዝዳንት ተሸከዲ መንግስት በበኩሉ የኮንጎ ወንዝ ጥምረት በሚል የትጥቅ ትግል እያደረገ ያለውን ቡድን ሶስት መሪዎች ያሉበትን ለጠቆመ አምስት ሚሊዮን ዶላር ካሳ እከፍላለሁ ብሏል፡፡
የቀድሞው የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ሀላፊ የነበሩት ኮርኔል ናንጋ የጥምረቱ መሪ ሆነው የተመረጡ ሲሆን በሀገሪቱ መንግስት የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል፡፡
የዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊፕ ተሸከዲ አሜሪካ በሩዋንዳ እና አማጹ ቢድኖቹ ላይ ጫና እንድታደርስ የዲፕሎማሲ ጥረት ከማድረግ ባለፈ ተጨማሪ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡
አማጺ ቡድኖቹን ለመደምስም የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚያደርግ ከሆነ ከሀገሪቱ ማዕድናት ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችልም እንደ አማራጭ ቀርቦላታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡