
ኤም23 እና የሩውዋንዳ ጦር በምስራቃዊ ኮንጎ ባደረሱት ጥቃት ከሶስት ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ500 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል
አሜሪካ በሩዋንዳ እና ኤም23 አማጺ ቡድን ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የተትረፈረፈ ማዕድን ባለቤት የሆነችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከባድ ጦርነት እየተካሄደባት ይገኛል።
ጦርነቱ ኤም23 የተሰኘው አማጺ ቡድን የፕሬዝዳንት ተሽከዲን መንግሥት በሀይል ለማስወገድ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
ኤም23 የተሰኘው እና በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰው አማጺ ቡድን ከሩዋንዳ ጦር ድጋፍ እንደሚደረግለት ይገለጻል።
ሩዋንዳ አማጺ ቡድኑን እየረዳሁ አይደለም ብትልም ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ግን ግልጽ ማስረጃ እንዳላቸው ይናገራሉ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ በኤም23 አማጺ ቡድን ላይ እና ሩዋንዳ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
የሩዋንዳ አካባቢ ውህደት ሚንስትር ጄምስ ካባሬቤ እና የኤም23 አማጺ ቡድን ቃል አቀባይ ላውረንስ ካንዩካ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሰዎች ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም መቀመጫቸው ለንደን እና ፓሪስ የሆኑ ሁለት ኩባንያዎችም በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል በሚል ነው።
ኤም23 አማጺ ቡድን በሩዋንዳ ጦር እርዳታ ጎማ እና ቡካቩ የተሰኙ ሁለት ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።
ካሳለፍነው ታህሳስ ወር ጀምሮ እየጨመረ በመጣው የምስራቅ ኮንጎ ቀውስ ምክንያት ከስድስት ሺህ በላይ ዜጎች ሞት እና አካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
እንዲሁም ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው እንደተፈናቀሉ እና 14 የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር አባላት መገደላቸውን አናዶሉ የተመድ ሪፖርትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።