ዲሞክራቲክ ኮንጎ አማጺያንን ለመዋጋት የቻድን ወታደራዊ እርዳታ ጠየቀች
ለአመታት ከመንግስት ጦር ጋር እየተዋጉ የሚገኙት የኤም 23 አማጽያን በሀገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎችን እየተቆጣጠሩ ነው

በወታደራዊ መንግስት የምትመራው የማዕከላዊ አፍሪካዊት ሀገር ለኮንጎ ጥያቄ በይፋ የሰጠችው ምላሽ የለም
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኤም 23 አማፂያን በምስራቃዊ ግዛቶቿ እያደረጉ ያሉትን መስፋፋት ለመግታት ቻድን ወታደራዊ ዕርዳታ ጠየቀች፡፡
የኤም 23 ታጣቂዎች በቅርብ ጊዜያት በማዕድን በበለጸጉት ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ኪቩ ስትራቴጂያዊ ስፍራዎችን እየተቆጣጠሩ ግስጋሴቸውን ቀጥለዋል፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ የኮንጎ ቀጠናዊ ውህደት ሚኒስትር ከቻድ ፕሬዝዳንት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ኢቲኖ ጋር ተገናኝተው ሲመክሩ በፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ ስም የድጋፍ ጥያቄውን ስለማቅረባቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የቻድ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳንቱ እና ሚኒስትሩ ባደረጉት ውይይት የወታደራዊ ድጋፍ ጥያቄው ከመቅረቡ ውጪ ዝርዝር የተወያዩባቸውን ጉዳዮች እና የተሰጠውን ምላሽ ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡
ሮይተርስ የቻድ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ ሀገሪቱ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ የቀረበላትን ጥያቄ እያጤነች እንደምትገኝ እና ምንም አይነት የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን አመላክቷል፡፡
የኮንጎ ባለስልጣናት ምንጮች በበኩላቸው ኪንሻሳ ከቻድ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ድጋፍን ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቧን አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የቻድ ፕሬዝዳንት ኮንጎን በመደገፍ ሉዓላዊነቷን እና ግዛቷን ማክበር ያለውን አስፈላጊነት በማጉላት ይፋዊ መግለጫ አውጥተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከጥር ወር ጀምሮ የኤም 23 አማፂያን የጎማ እና ቡካቩ ከተሞችን ጨምሮ በሰሜን ኪቩ እና በደቡብ ኪቩ ግዛቶች ዋና ዋና ስፍራዎችን ተቆጣጥረዋል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለስልጣናት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤም 23 ታጣቂዎች በሩዋንዳ ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢከሱም ኪጋሊ ግን ውንጀላው ከእውነት የራቀ ነው በሚል አስተባብላለች፡፡
ሩዋንዳ በኮንጎ እና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ጦርነት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም አማጺያኑ ከተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች የሚገኙ ማዕድናትን በማዘዋወር በራሷ ስም ለገበያ እያቀረበች እንደምትገኝም ትከሰሳለች፡፡
በኮንጎ ከ20 ዓመታት በላይ በዘለቀው ግጭት ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡