የጸጥታው ምክርቤት የኤም23 አማጺያን ከዲአር ኮንጎ እንዲወጡ አሳሰበ
በምስራቃዊ ኮንጎ የሚካሄደውን ጦርነት በሚያራዝሙ አካላት ላይ ማዕቀብ እንደሚጥልም አስጠንቅቋል

በሩዋንዳ ድጋፍ የሚደረግላቸው የኤም23 አማጺያን በርካታ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት የኤም23 አማጺያን በምስራቃዊ ዴሞክራሲያዊ ኮንጎ ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ አሳሰበ።
ምክርቤቱ በፈረንሳይ አማካኝነት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ትናንት አጽድቋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላስ ደ ሪቬሪ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሉአላዊነት ሊከበር ይገባል ያሉ ሲሆን፥ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረስም ጠይቀዋል።
የውሳኔ ሃሳቡ የሩዋንዳ ጦር ለኤም23 አማጺያን የሚያደርገውንን ድጋፍ እንዲያቋርጥ እና ከኪንሻሳ ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቅ ነው።
የጸጥታው ምክርቤት አባል ሀገራት ተወካዮች የሩዋንዳ ጦር ለአማጺ ቡድኑ "በቀጥታ ድጋፍ አድርጓል" ሲሉ መናገራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። ኪጋሊ ግን በኪንሻሳ እና ምዕራባውያን ሀገራት የሚቀርብባትን ወቀሳ በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ከርስ በርስ መካሰስና ግጭት ወጥተው ወደ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንዲመለሱ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ጠይቋል።
ምክርቤቱ የምስራቃዊ ኮንጎውን ጦርነት በሚያባብሱና በሚያራዝሙ አካላት ላይ ማዕቀብ ለመጣልም ዝቷል።
አሜሪካ በሩዋንዳ ሚኒስትርና በኤም23 አማጺ ቡድን አመራሮች ላይ ትናንት ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
"የማዕድን መሬት ወረራ"
በሺዎች የሚቆጠሩ የኤም23 አማጺያን በማዕድን ሃብት በበለጸገው የምስራቃዊ ኮንጎ በርካታ ከተሞችን እየተቆጣጠሩ ነው።
ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ በሰሜን እና ደቡብ ኪቩ ግዛቶች ላይ አነጣጥረው በጀመሩት ውጊያ የሁለቱንም ግዛቶች ዋና ከተሞች መቆጣጠር ችለዋል።
አማጺያኑ ማሲሲ፣ ሳኬ እና ንያቢብዌ የተባሉ ወሳኝ ከተሞችን ተቆጣጥረውም አስተዳደራዊ መዋቅር መዘርጋት መጀመራቸው ተነግሯል።
የመንግስታቱ ድርጅት የምስራቃዊ ኮንጎ ተልዕኮ መሪ ቢንቱ ኬይታ፥ አማጺያኑ መዲናዋን ኪንሻሳ የመቆጣጠር ፍላጎታቸውን በተደጋጋሚ እየገለጹ ነው ብለዋል።
ሩዋንዳ ጎረቤቷ ዲአር ኮንጎ "ኤፍዲኤልአር" የተባለውን የሩዋንዳ ታጣቂ ቡድን የጦር መሳሪያ እያስታጠቀች ነው በሚል ትከሳለች። የሁቱ ታጣቂ ቡድኑ ከ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ጋር ግንኙነት እንዳለውም ትገልጻለች።
ኪጋሊ ኤም23 አማጺ ቡድንን የምትደግፈው የኪንሻሳን የማዕድን ስፍራዎች ለመቆጣጠር በማለም እንደሆነ ቢነገርም ማስተባበሏን ቀጥላለች።
በምስራቃዊ ኮንጎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ከ270 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው የገለጸው የመንግስታቱ ድርጅት የፍልሰተኞች ኤጀንሲ፥ ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ ለማቅረብ ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ ያስፈልገኛል ብሏል።